የምሥራቅ፣ ምዕራብና ደቡብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የ፳፻፱ ዓ/ም የሥራ ክንውን ዘገባ

እንደሚታወቀው ፳፻፱ ዓ/ም የሥራ ዘመን በሀገረ ስብከታችን ታሪክ በልዩ ሁኔታ ሲዘከር የሚኖር የሥራ ዘመን ነው። ልዩ የሚያደርገውም ቀደም ሲል በሀገረ ስብከቱ ውስጥ በልዩ ልዩ ኃላፊነት በማገልገል ላይ ከሚገኙት አባቶች መካከል እንደአገልግሎት ዘመናቸውና እንደ አገልግሎት ፍሬያቸው ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ትምህርታቸውንና አገልግሎታቸውን በዝርዝር የሚያስረዳ ሰነድ አዘጋጅቶ ለኤጲስ ቆጶስነት ምርጫ በእጩነት ካቀረባቸው ፮ አባቶች መካከል ፫ቱ የቅዱስ ሲኖዶስን ይሁንታ አግኝተው መመረጣቸውና ለመዐርገ ጵጵስና መብቃታቸው ሲሆን ሀገረ ስብከታችን ለእነዚሁ ለሌሎቹም በአንዲት ጉባዔ ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ከፍ ያለ ኃላፊነት ለጣለችባቸው ብፁዓን ጳጳሳት ሁሉ ዘመነ ጵጵስናቸው መልካም ፍሬ የሚያፈሩበት ይሆንላቸው ዘንድ ከልብ ይመኛል።

በመቀጠልም የሀ/ስከቱ አስተዳደር ጽ/ቤት በሥራ ዘመኑ በማእከል ደረጃ እንዲሁም በሀገረ ስብከቱ ሥር ያሉ አድባራትን በማስተባበር ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ዋና ዋናዎቹን እንደሚከተለው እናቀርባለን።

1. ከቅዱስ ሲኖዶስ እና ከመንበረ ፓትርያርክ የሚተላለፉ መመሪያዎች ጉዳዩ በሚመለከታቸው የሀገረ ስብከቱ ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎችና በሀገረ ስብከቱ አድባራት ተግባር ላይ እንዲውሉ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ መመሪያዎቹ ተፈጻሚነት እንዲያገኙ ተደርጓል። በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የሚከሠቱ ሁኔታዎችንም በመከታተል ተገቢውን መመሪያ በማስተላለፍና እንደአስፈላጊነቱም ምእመናን ዐውቀዉት የበኩላቸውን ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉ ጥረት ተደርጓል።
2. በየደብሩ የሚሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲጠናከር፣ ትምህርተ ወንጌል እንዲስፋፋ፣ ሰ/ት/ቤቶች እንዲደራጁ ጥረት ለአድባራትም ድጋፍ እየተደረገ ሲሆን በተለይ ሰ/ት/ቤቶችን በተመለከተ ለክትትልና ተገቢውን እገዛ ለማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ሰ/ት/ቤቶችን በየአካባቢያቸው እርስ በርሳቸው ተቀራርበው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግና ሥርዓት የጠበቀ ተመሳሳይ አደረጃጀትና አካሄድ እንዲኖራቸው ትምህርትና ሥልጠና እንዲያገኙ፣ ልምድ እንዲለዋወጡ የሚያስችል ማእከል በሀ/ስ/ከቱ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ኖሯቸው በጋራ እየተመካከሩ እንዲሠሩ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተጀመረ ሲሆን በተገባደደው የሥራ ዘመን በጀርመን የተጀመረው ሙከራ ከሞላ ጎደል ውጤታማ በመሆን ላይ ይገኛል። በቀጣዩ የሥራ ዘመንም እንቅስቃሴው በሌሎቹም የሀ/ስከቱ አካባቢዎች የሚቀጥል ይሆናል።
3. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክናን እምነት፣ ሥርዓት፣ ታሪክና ትውፊት የሚያስረዳ መጽሐፍ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች አዘጋጅቶ በማሠራጨት በአውሮፓ ተወልደው ለሚያድጉና የአማርኛ ቋንቋ በአግባቡ መረዳት የማይችሉ እንዲሁም ከሌላ እምነት የሚመለሱ የሌሎች ሀገሮች ዜጎች ስለ ቤ/ክኒቱ እምነትና ሥርዓት ለማወቅ ለሚያቀርቡት ጥያቄ ምላሽ መስጠት ተገቢ መሆኑን በማመን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስ በ፲፱፻፸፪ ዓ/ም ያዘጋጀውን አጭር የሥርዓት መጽሐፍ በመጀመመሪያ ዙር ወደጀርመንኛና ወደ ፈረንሳይኛ ለመተርጎም የተጀመረው ሥራ በአብላጫው ተጠናቋል። በ፳፻፲ዓ/ም ቀሪው ጥቂት የትርጉምና የአርትዖት ሥራ ተጠናቆ የሚሠራጭ ይሆናል።
4. ትምህርተ ወንጌልን ከማስፋፋት ጋር በተያያዘ በሰ/ት/ቤት መደበኛ መርሐ ግብሮች ላይ ወጣቶችን የሚያስተምሩ ዲያቆናትና ወጣት መዘምራን ዕውቀታቸውን አጎልምሰው በተሻለ ሁኔታ ማገልገል ይችሉ ዘንድ ለማዘጋጀት ታስቦ ፩ኛ ዙር የርቀት ትምህርት ሥልጠና ከመስከረም — የካቲት ወር ፳፻፱ ዓ/ም ድረስ ለስድስት ወራት በታወቁ መምህራን የተሰጠ ሲሆን ሥልጠናውን ሙሉ በሙሉ የተከታተሉ ከተለያዩ አድባራት የተወከሉ ፰ ደቀመዛሙርት በመጋቢት ወር ፳፻፱ ዓ/ም በሰርተፊኬት ተመርቀዋል። ፪ኛ ዙር ሥልጠና በዚሁ ዓመት ለመስጠት ታስቦ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በታሰበው ጊዜ መጀመር ባለመቻሉ ወደቀጣዩ የሥራ ዘመን እንዲሸጋገር ተደርጓል።
5. በሀገራችን ከድርቅ ጋር ተያይዞ በተከሠተው ረሀብ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳትና መልሶ ለማቋቋም ቅዱስ ሲኖዶስ ባስተላለፈው ጥሪ መሠረት በየቤ/ክኑ ጸሎተ ምሕላ እንዲደረስና የርዳታ ገንዘብ እንዲሰበስብ ሠርኩላር በማስተላለፍና የቅርብ ክትትል በማድረግ ከ፲፱ አድባራት ፲፱፼፰፪ /አስራ ዘጠኝ ሺህ ስድሳ ሁለት ኦይሮ/ (476,550,00 ብር) ተሰብስቦ ቅዱስ ሲኖዶስ ወዳቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ በባንክ የተላለፈ ሲሆን ከመ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት የተጻፈ የማረጋገጫና የምስጋና ደብዳቤ ለአድባራቱ እንዲደርስ ተደርጓል።
6. የራስ የሆነ ሕንፃ ቤ/ክ ለመግዛት ወይም ለመገንባት በሀገረ ስብከቱ ዕውቅና የተሰጠው እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ አድባራት መካከል አንዱ የሆነው በሮም የደ/ከ ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ በ፫፻ ሺህ /ሦስት መቶ ሺህ/ ኦይሮ የሕንፃ ቤ/ክ ግዢ የፈጸመ ሲሆን የቁልፍ ርክክቡ ስነ ሥርዓት በጥር ወር ፳፻፱ ዓ/ም የሀ/ስከቱ ሊቀ ጳጳስ እና ም/ሥራ አስኪያጅ በተገኙበት ተፈጽሟል።
7. በየካቲት ወር ፳፻፱ ዓ/ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አቀፍ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ባደረገላቸው ጥሪ መሠረት በጄኔቫ ባደረጉት የአራት ቀናት ቆይታ በጄኔቭ የሚገኙት አጥቢያ አ/ክናት ከሀ/ስከቱ ሊቀ ጳጳስ ጋር ተገቢውን አቀባበልና አሸኛኘት ያደረጉ ሲሆን ቅዱስነታቸውም በተደረገላቸ አቀባበል ደስ መሰኘታቸውን ገልጸዋል።
8. ለመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክህነት የሚደረገው ዓመታዊ ፈሰስ ካለፈው የሥራ ዘመን በሁለት እጥፍ አድጎ እንዲከፈል ተደርጓል።
9. የአዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን መቋቋም በተመለከተ በሥራ ዘመኑ ፫ የጽዋ ማኅበራት ታቦተ ሕግ ገብቶላቸው ከጽዋ ማኅበርነት ወደ አጥቢያ አ/ክናትነት እንዲሸጋገሩ በእቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን የሁለቱ ማለትም የብሬመን ቅዱስ እስጢፋኖስ – ጀርመን እና የልዮ ቅዱስ ገብርኤል – ፈረንሳይ ቅዳሴ ቤት መርሐ ግብር በልዩ ልዩ ምክንያት በታቀደው መሠረት ሳይፈጸም የቀረ ሲሆን ከ፲ ዓመታት በላይ ከአጎራባች አድባራት በሚላኩ ንዋያተ ቅድሳትና ልኡካን አልፎ አልፎ አገልግሎት ሲሰጥበት የቆየው የፍሬንሲ ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ – ጣልያን ሰኔ ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ቅዳሴ ቤቱ ተከብሮ ወደ አጥቢያ ቤ/ክንነት ተሸጋግሯል። ከላይ የተጠቀሱት የሁለቱ አ/ክናት ቅዳሴ ቤት በቅርቡ የሚከበር ይሆናል።
10. በአገልግሎት ዘመኑ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ለ፬ ደቀመዛሙርት የዲቁና እና ለ ፩ ዲያቆን የቅስና መዐርግ ሰጥተዋል።
11. በአገልግሎት ዘመኑ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት ክርስትና የተነሡ ሲሆን ፫ ከሌላ እምነት የተመለሱ ወጣቶች አምነው ተጠምቀዋል።
12. መንበረ ጵጵስና ሆኖ ለቤ/ክኒቱ እንደ ማእከል የሚያገለግል ሕንፃ በጀርመን ካሉ ነባር አ/ክናት በስጦታ ለማግኘት ጥረት ተደርጓል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በመጋቢት ወር ፳፻፱ ዓ/ም ከካቶሊካዊት ቤ/ክ የአይሽቴት ሀገረ ስብከት ጳጳስና ከሀ/ስከቱ የስደተኞች ጉዳይ ኃላፊ ጋር የተደረገው ውይይት ተስፋ ሰጪ የነበረ ሲሆን ሀገረ ስብከታችን በተገባለት ቃል መሠረት በቀጣይ ፪ ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተገባለት ቃል እንደሚፈጸምለት በተስፋ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።

ሀገረ ስብከታችን በ፳፻፱ ዓ/ም ካከናወናቸው ተግባራት መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱት ከዚህ በላይ በቅደም ተከተል የተጠቀሱት ሲሆኑ በ፳፻፲ ዓ/ም ሊያከናውናቸው ካቀዳቸው እቅዶች መካከል አንኳሮቹ የሚከተሉት ናቸው፦

1. የተጀመረውን የመጽሐፍ ትርጉምና አርትዖት ሥራ አጠናቆ መጽሐፉን በአድባራት በኩል ለተጠቃሚዎች ማድረስ፤
2. የቅዳሴ ቤት አከባበር መርሐ ግብር ለተራዘመባቸው ሁለት የጽዋ ማኅበራት አጭር ተለዋጭ መርሐ ግብር መያዝና ቅዳሴ ቤት ተከብሮላቸው ወደ ቤ/ክንነት እንዲያድጉ ማድረግ፤
3. ለዲያቆናትና ለሰ/ት/ቤት አስተባባሪዎች የሚሰጠውን የርቀት ትምህርት ሥልጠና መርሐ ግብር አጠናክሮ በመቀጠል አዳዲስ ረዳት አገልጋዮችን ማፍራት፤
4. የራሳቸው የሆነ ሕንፃ ቤ/ክ ለመገንባት ወይም ለመግዛት ትረት ለሚያደርጉ አድባራት እንደ ቅደም ተከተላቸው ተገቢውን እገዛ ማድረግ፤
5. ለመንበረ ጵጵስና የተሰጠውን ተስፋ ተከታትሎ ማስፈጸም።

ሀገረ ስብከታችን በልዑል እግዚአብሔር አጋዥነት ከዚህ በላይ የተገለጹትንና ተመሳሳይ ተግባራትን እንዲሁም መደበኛ አገልግሎቶችን በአግባቡ ለማከናወን ጸሎታችሁ፤ ምክራችሁና ድጋፋችሁ እንዳይለየው ይማጸናል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *