“ተፋቀሩ ዘልፈ እስመ ማእሠረ ተፍጻሜቱ ውእቱ — ዘወትር በፍቅር ኑሩ የመጨረሻው ማሠሪያ እሱ ነውና።” ቆላ ፫፥፲፬

የብፁዕ አቡነ ሙሴ

የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የመላው አውሮፓ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳን

መስከረም ፳፻፲ ዓ/ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

የተከበራችሁ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ምእመናንና ምእመናት እንዲሁም የሰ/ት/ቤት ወጣት መዘምራን መዘምራት፥ ቸርነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ የዕለታትና የዓመታት የጊዜያት ሁሉ ባለቤት በአንድነት በሦስትነት ሲመሰገን የሚኖር አምላካችን እንኳን ሁላችንንም በሰላምና በጤና ጠብቆ ከዘመነ ማቴዎስ ወደዘመነ ማርቆስ አሸጋገረን! አዲሱን ዘመን የምሕረትና የይቅርታ የሰላምና የበረከት ዘመን ያድርግልን።

ከላይ በመግቢያዬ የጠቀስሁት አምላካዊ ቃል ሐዋርያ ሰላም መምህረ አሕዛብ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ በወህኒ ቤት ታሥሮ ሳለ በቆላስይስ ለነበሩ በኤጳፍራስ ትምህርት ካለማመን ወደማመን ለመጡ በተማሩትም ትምህርት ጸንተው አምላካቸው እግዚአብሔርን በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ሲያገለግሉት ለመኖር ቁርጠኛ አሳብ ለነበራቸው ከቅዱሳንም ጋር ለትምህርተ ወንጌል መስፋፋት ለሃይማኖተ ክርስቶስ መበልጸግ ይተጉ ለነበሩ ምእመናነ ወንጌል ከሃይማኖት ከበጎ ሥራ ፈቀቅ የሚያደርግ እንቅፋት ሳይገጥማቸው በበረከት ላይ በረከት በጸጋ ላይ ጸጋ እየተጨመረላቸው ይኖሩ ዘንድ ለመምከርና ለማትጋት ጽፎ ከላከላቸው ቃለ ምዕዳን ውስጥ የተገኘ አምላካዊ ቃል ነው።
ሐዋርያው መልእክቱን የሚጀምረው የምእመናኑን እምነት፣ በጎነት፣ ደግነት፣ ትጋትና የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት መትጋታቸውን በተወደደ ቃል በማመስገን ነው። አያይዞም ይህ ስለነርሱ በቅዱሳን የሚነገርላቸውና የሚመሰከርላቸው ጽኑ እምነታቸውና በጎ ሥራቸው እንዳይጠፋና እንዳይለወጥ ሁሉን ወደሚችል አምላክ ትዕግሥትን ጽናትን ያድላቸው ዘንድ እንደሚጸልይላቸው ገልጿል። በመቀጠልም የጽሑፉ ዓላማ የሐዋርያም ተልእኮው ምእመናን ከእምነታቸው ሳይናወጡ ለእግዚአብሔር መንግሥት የሚያበቃቸውን ምግባር ትሩፋት በመሥራት እንዲጸኑ መምከር ማስተማር ነውና ይመክራቸዋል። በምክሩም በሃይማኖት ለሚኖር ሰው የእምነቱም የትሩፋቱም መጠቅለያው መደምደሚያው ፍቅረ እግዚአብሔር ፍቅረ ቢጽ ነውና “ወምስለ ዝንቱ ኵሉ ተፋቀሩ ዘልፈ እስመ ማእሠረ ተፍጻሜቱ ውእቱ — ከዚህም ሁሉ ጋር ዘወትር በፍቅር ኑሩ የመጨረሻው ማሠሪያ እሱ ነውና” ሲል ከማመናቸው፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ከመትጋታቸውና በጎ ለመሥራት ከመሽቀዳደማቸው ይህንንም ከመሰለው አገልግሎታቸው ሁሉ ጋር ፍቅርን ተጎናጽፈው ፍቅርን ተቀዳጅተው ሊኖሩ እንደሚገባቸው አጉልቶ ነግሯቸዋል።

መምህሩ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ፍቅር ከትእዛዛት መካከል የሚበልጣት እንደሌለ፥ የበግ ጠቦት ወይም የሚቃጠል መሥዋዕት ከማቅረብም የምትልቅ የሃይማኖት መገለጫ የበጎ ሥራም መቋጫ እንደሆነች ሲያስረዳ “ወዝንቱ ይኄይስ እምኵሉ መባእ ወእምኵሉ መሥዋዕት — ይህም ከመባ ከመሥዋዕትም ሁሉ ይበልጣል” ብሏል። ሉቃ ፲፪፥፴፫ ዳግመኛም ስለሰው ልጆች መዳን ራሱን ለሕማም ለሞት አሳልፎ መስጠቱ ለሰው ልጆች ካለው አምሳያ የሌለው ፍጹም ፍቅሩ የተነሣ መሆኑን በቅዱስ አንደበቱ “እስመ ከመዝ አፍቀሮ እግዚአብሔር ለዓለም እስከ ወልዶ ዋሕደ መጠወ ወወሀበ ቤዛ — እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና” ሲል አስረግጦ ነግሮናል። ዮሐ ፫፥፲

ሰው ምንም ያህል በእግዚአብሔር አምላክነት ቢያምን፤ ሊያገለግለውና ሊያመልከውም ምንም ያህል ራሱን ቢያዘጋጅ እግዚአብሔር ያደረገለትን ይህን የመሰለ ከደግነት የላቀ ደግነት ከለጋስነት የላቀ ለጋስነት ለእግዚአብሔር ሊያሳይና ሊያደርግ አይችልም። ማድረግ የተቻለውን መሆንም የሚቻለውን ያህል ግን በፍቅር ሆኖ ቢያደርግ የአቤልን መሥዋዕትና ደግነት ያህል እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኘው በርግጥ ይችላል። ፍቅር ደግነት ነው፣ ፍቅር የዋህነት ነው፣ ፍቅር ቅንነት ነው፣ ፍቅር ለጋስነት ነው፣ ፍቅር ታማኝነት ነው፣ ፍቅር መንፈሳዊ ኃይል ነው። እስራኤል ዘሥጋን ከፍቅር የተለየ ግዝረታቸው ከሞት አላዳናቸውም፤ እኛንም ፍቅር ያልታከለበት ጥምቀታችን ለእግዚአብሔር መንግሥት የሚያበቃ ምግባር ትሩፋት ለመሥራት አይረዳንም። ሐዋርያትን እስከ ምድር ዳርቻ ዞረው ስለእግዚአብሔር መንግሥት እንዲሰብኩ መገፋቱን፣ መራብ መጠማቱን እንዲታገሡት ኃይል የሆናቸው በልባቸው የታተመው ፍቅር ነው። ሰማዕታትንም ከዐላውያን ነገሥታት ከዐላውያን መኳንንት ፊት ቀርበው ስለሃይማኖታቸው መስክረው ሰውነታቸውን ለእሳት አንገታቸውን ለስለት እንዲሰጡ ያስጨከናቸው በልባቸው የሚንቦገቦገው የፍቅር ነበልባል ነው። ጻድቃንን ዓለምን ንቀው ድምፀ አራዊቱን ፀብአ አጋንንቱን ታግሠው በተጋድሎ እንዲኖሩ ያጸናቸው በአካላቸው የተዋሐደው ፍቅረ እግዚአብሔር ነው። ፍቅርን እንደ ግምጃ ባይለብሱት እንደ አክሊል ባይቀዳጁት ኖሮ ሐዋርያቱም በምድር ዳርቻ ባልተገኙ፣ ሰማዕታትም ከከሀዲዎች ጋር ባልተፋጠጡ፤ ጻድቃንም ወደ በረሀ ባልፈለሱ ነበር። ሥጋን ከለበሱ ዘንድ የማይቀር ሞታቸው ዕረፍታቸው ክብራቸው ተድላቸው እንዲሆንላቸው አምላካቸውን ደስ ማሰኘት የተቻላቸው ተስፋቸውም፣ እምነታቸው፣ ተጋድሎአቸውም፣ ትሩፋታቸውም ሁሉ በፍቅር ተጀምሮ በፍቅር የተፈጸመ ስለሆነ ነው። ቅዱሳን ስለአምላካቸው ክብር ቀንተው መከራ ሲቀበሉ በልባቸው የተሳለው ፍቅረ እግዚአብሔር ይገለጣል፣ ስለነፍሳት መዳን በጸሎትና በምልጃ ነፍሳቸውን ሲያስጨንቋት በልባቸው የታተመው ፍቅረ ቢጽ ይታወቃል። ፍቅራቸውን የገለጡበት መንገድ ይህ ብቻ ነው፣ ከዚህ በተለየ መልኩ ለአምላካቸውም ለወገኖቻቸውም ፍቅር እንዳላቸው የገለጡበት መንገድ የለም። የአምላካቸውን ፍለጋ ተከትለው እርሱ ለሰዎች ያለውን ፍጹም ፍቅሩን ደሙን በማፍሰስ እንደገለጠው እነርሱም መከራን በመታገስ ፍቅራቸውን ገለጡት።

እግዚአብሔር ይህን ትእዛዝ የሠራው ለተለዩ ሰዎች አይደለም። ከአዳም ወገን የተወለደ የሰው ዘር ሁሉ ፍቅር በልቡ ቦታ እንዲኖረው ይፈልጋል። ሁሉ በሰማዕትነት ደሙን እንዲያፈስ፣ ሁሉ ለአራዊት እንዲጣል፣ ሁሉ ከእሳት እንዲወረወር አይደለም የሚጠብቀው። በፍቅር ሆኖ አቡነ አቡነ ብሎ ስሙን የሚጠራው በእርሱ ዘንድ በእውነት እንደ ሰማዕት ነው፤ በፍቅር ሆኖ ለአምልኮቱ መግለጫ ቀጭን ጧፍ የሚያቃጥልለት ለእርሱ ንጹሑን መገበርያ እንደሠዋለት እንደ አቤል ነው፤ በፍቅር ሆኖ በስሙ ደኃውን ጦም አዳሪውን የሚጠይቅለት እንግዳ በመቀበሉ እንደከበረው እንደ አብርሃም ነው። ፍቅር የሌለበት ቅዳሴ፣ ውዳሴ፣ ዝክር፣ መባእና መሥዋዕት ይህን የመሰለው ሁሉ ግን የሰው ፍቅር ምግባቸው የሆኑ የእግዚአብሔርን ዓይኖች የሚስብ ሊሆን አይችልም። ቅዱስ ጳውሎስ በተመሳሳይ ርእሰ ጉዳይ ለቆሮንቶስ ምእመናን በጻፈው መልእክቱ ላይ “ወእመኒ ብየ ኵሉ ሃይማኖት እስከ አፈልስ አድባረ ወተፋቅሮ አልብየ ከንቶ ኮንኩ — ተራራ እስከማፍለስ የሚያደርስ ፍጹም ሃይማኖትም ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ሆንኩ” ፩ ቆሮ ፲፫፥፪ ማለቱ ከዚህ የተነሣ ነው።

ወገኖቼ! በሃይማኖት ስንኖር ሃይማኖታችን ለሕይወት የሚያበቃ ምግባር ትሩፋታችን በረከትን የሚያሰጥ የሃይማኖት ተግባር እንዲሆንልን በፍቅር ልንኖር በፍቅር ልንመላለስ ያስፈልጋል። እግዚአብሔርን መውደድ በልባችን ሳይኖር የምናምነው እምነት ምን ሊረባን ይችላል? ለሰዎች ፍቅር ሳይኖረን የምናደርገው ችሮታ ከዝና በቀር ምን ዓይነት በረከት ያስገኝልናል? ሰዎች በዚህ ዓለም ስንኖር እርስ በርሳችን ተስማምተንና ተከባብረን፣ ተጋግዘንና ተደጋግፈን ልንኖር ይገባናል እንጂ እርስ በርሳችን በመጠላላትና በልዩ ልዩ ሰው ሠራሽ የመለያያ ዘዴዎች እየተቧደንን የእገሌ የእገሌ እየተባባልን አልፎ ተርፎም እየተጎዳዳን የምንኖር ከሆነ ስንኳን የወዲያኛውን ዓለም ይህችንም ምድር በአግባቡ ልንኖርባት አንችልም። ይህም የሰውን ህላዌ ከእንስሳት የሚያሳንስ ክፉ ጠባይ እንጂ የሚያኮራ ተግባር አይደለም። ፍቅር ሰላም ነው፣ ፍቅር ጸጥታ ነው፣ ፍቅር ዕረፍት ነው፣ ፍቅር ደስታ ነው። እርስ በርሳችን የምንዋደድ ብንሆን እኮ በስጋት ማደር፣ በዘብ መጠበቅ፣ መሣሪያ መታጠቅ ባላስፈለገን፥ ይልቁንም ሰልፋችን ሁሉ እንደኛ ካሉ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ጋር መሆኑ ቀርቶ የሰውን ልጅ በአጠቃላይ ከሚጣሉና ከሚተነኩሉ ከአጋንንት ሠራዊት ጋር ብቻ በሆነ ነበር። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እርስ በርስ መዋደድ ማንንም የጎዳበት ማንንም ያከሰረበት ጊዜ የለም። የፍቅር መታጣት ግን ዓለምን ለእሳትና ለንፍር ውኃ ለነፋስና ለማዕበል ለቸነፈርና ለረሀብ ሲያጋልጥ ምድርን በመቅሠፍት ሲያስገርፋት ነው የኖረው አሁንም ያለው። እንግዲህ እስከመቼ ድረስ ጣዕም የሌለው ለዛቢስ ኑሮ እንኖራለን? እስከመቼስ የሰማዩን ቤታችንን በላያችን ላይ እንዲዘጋብን እንጥራለን? የእግዚአብሔር ጽድቅ ለመሥራት ፍቅረ እግዚአብሔር ያስፈልገናል፤ የነፍስ ስንቅ ለመያዝ ፍቅረ ቢጽን መያዝ ይገባናል። ስለዚህም ጥላቻን፣ መለያየትን፣ መከፋፈልን፣ መቀያየምን ከልባችን አስወግደን አምላካችን እግዚአብሔርን በመውደድ የእጁ ሥራዎች ከሆኑ የአዳም ልጆች ሁሉ ጋር እርስ በርስ በመዋደድ ልንኖር ይገባናል።

የሰላም ባለቤት የፍቅር አምላክ ሁላችንንም ይባርከን! ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በቸርነቱ ይጠብቅልን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *