የብፁዕ አቡነ ሙሴ ቃለ ምእዳን ፳፻፱ ዓ/ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

የተወደዳችሁ አዕይንት እግዚአብሔር ካህናት እና አባግዐ ክርስቶስ ምእመናን፤ ቸርነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር እንኳን በሰላምና በጤና ጠብቆ ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ አሸጋገራችሁ፤ አዲሱ ዘመን የሰላምና የበረከት ዘመን ይሁንላችሁ።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንከሰ ጽንዑ በእግዚአብሔር ወበጽንዐ ኃይሉ ወልበሱ ወልታ እግዚአብሔር በዘትክሉ ተቃውሞቶ ለመናስግተ ሰይጣን“ ትርጉም “ከእንግዲህስ ወዲህ በእግዚአብሔር ጽኑ፤ በኃይሉም ጽናት፤የሰይጣንንም ማሳት ታቸንፉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ጋሻ ልበሱ“ ሲል የኤፌሶንን ምእመናን ሰይጣን በተንኮል ከሚያመጣባቸው ጦር የሚድኑበት ብሎም ድል የሚነሡበትን የእግዚአብሔርን ጋሻ ገንዘብ እንዲያደርጉ መክሯቸዋል። ኤፌ ፮፥፲ ሐዋርያው ይህንን ምክር የመከራቸው ምእመናን በሥጋ ዓለም እንደሚደረገው ላለ ሥጋዊ ጦርነት ለማዘጋጀት አይደለም። ምእመናን በዓለም ሲኖሩ ክርስቶስን መስለን በሃይማኖት በምግባር ጸንተን እንኖራለን ስላሉ በዚህም ዓላማቸው ለሰይጣንና ለመልእክተኞቹ አጋንንት መገዛትን ስለካዱ የሚገጥማቸው ብዙ የሰይጣን መፈታተን መተነኳኮልና መከራ ያገኛቸው ዘንድ አይቀርምና ለመንፈሳዊ ሰልፍ በእምነት እንዲዘጋጁ ለማስጠንቀቅ ነው። ሰልፉም ሰውን ከማሳት በቃኝ ከማይል ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር እንጂ ከሥጋዊ ደማዊ ፍጥረት ጋር አለመሆኑ ሲገልጽ “እስመ ቀተልክሙ ኢኮነ ምስለ ዘሥጋ ወደም“ ትርጉም “ሰልፋችሁ ከሥጋዊ ከደማዊ አርበኞች ጋር አይደለምና“፤ “ዘእንበለ ምስለ መኳንንተ ጽልመት ወአጋንንት እኩያን እለ መትህተ ሰማይ“ ትርጉም “ዓለመ ጽልመትን ከሚገዙ ከአጋንንት ጋር ነው እንጂ“ ብሎ አስታውቋል። ሰው ከሰው ጋር የሚ ያደርገው ጦርነት በሥጋዊ ሰልፍ የሚሰለፉበት ቀላል ጦርነት ነው፤ ከአጋንንት ጋር የሚደረገው ጦርነት ግን በሥጋዊ ኃይል አቸናፊ የሚሆኑበት ጦርነት አይደለም። በዚህ ውጊያ ለማሸነፍ የሃይማኖት ኃይል ያስፈልጋል። ሐዋርያው “ወልበሱ ወልታ እግዚአብሔር“ ማለቱ ስለዚህ ነው። የጨለማውን ገዢ ሰይጣንን መልእከተኛው ዓለምንም ድል የሚነሣው በእምነት የጸና ብቻ ነውና “ወመኑ ውእቱ ዘይመውዖ ለዓለም ዘእንበለ ዘየአምን ከመ ኢየሱስ ውእቱ ወልደ እግዚአብሔር“ ትርጉም “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን ማቸነፍ የሚቻለው ማን ነው“ እንዲል። ፩ ዮሐ ፭፥፭

ኢዮብ ከእግዚአብሔር ጋር ሊያጣላው የታገለውን ባላጋራውን ሰይጣንን ታግሎ አቸንፎታል፤ በጠጠር ግን አይደለም ዳዊት ጎልያድን እንዳሸነፈ። የኢዮብ ወንጭፉም ጠጠ ሩም ትዕግሥት ነበረች። በሃይማኖት የለዘበች የጠነከረች ትዕግሥት፤ በዚህ አሸንፎታል። ይህንን ድል ሰዎች ሁላችን ልንቀዳጀው እንችላለን። ሃይማኖትንና የሃይማኖት አበጋዞች ትዕግሥትን፣ የዋሃትንና ፍቅርን ከለበስን ከተጫማን። ከውጪ የሚመጣውን ጠላት ለመከላከል ለማቸነፍ የሚያስፈልገው የውጊያ ስልት መጀመሪያ የራስን ጠባይ ማዘዝ፣ የሥጋን አሳብ መግዛት፣ የሥጋ መሻት ድል መንሣት ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ እንዲጠብቅ ሰውነታችንን ካስለምደነው ከዚያ በኋላ የሚመጡ ፈተናዎችን መመለስ ቀላል ነው። ትልቁ ትግል ከራስ ጋር የሚታገሉት ትልቁም ድል ራስን በማሸነፍ የሚገኝ ድል ነውና። ራሱን መግዛት የቻለ ሰው በዓይናማ ሰው ሊመሰል ይችላል፤ ሰው ዓይኑ ብርሃን ለማየት ጤናማ ከሆነለት ከጉድጓድ አይወድቅም ገደል አይጠልቅም። ራሱን መግዛት የቻለም ሰው የወዲያኛውን ዓለም እያየና እየናፈቀ ከትሩፋት ወደ ትሩፋት ይሸጋገራል እንጂ በኃጢአት ገደል አይወድቅም ወደሲኦልም አይጠልቅምና።

ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “እስመ ጸላእክሙ ጋኔን ይጥህር ከመ አንበሳ ወይኀሥሥ ዘይውሕጥ“ ትርጉም “የሚሰብ ረውን እንደሚሻ አንበሳ ጠላታችሁ ጋኔን ጣህሩን ያሰማል“ ሲል የዚህን ባላጋራ ዕረፍት የለሽ ወረራና አደን በአንበሳ መስሎ በመግለጽ ተግተን ነቅተን እንድንጠበቅ ይመክ ረናል። ፩ ጴጥ ፭፥፮ አንበሳ ርቦት ድምጹን ሲያሰማ እንስሳት ከድንጋጤ የተነሣ ወዳለበት ይሄዳሉ። ሰውም ኃጢአትና በደል የሰይጣን ሥራ መሆኑን እያወቀም ቢሆን በመዘናጋት በድፍረት ይሠራዋል፤ አንበሳ ኃይለኛ ነው ሥጋ ሳይበላ አያድርም ሰይጣንም ሰውን ሳያስትና ሳይጎዳ አይውልም። ስለዚህም ሐዋርያው አያይዞ “ወይእዜኒ ፍርህዎ ለእግዚአብሔር ወአምላክዎ በጽድቅ ወበርትዕ“ ትርጉም “እንግዲህ እግዚአብሔርን ፍሩት፤ በእውነትና በቅንነትም አምልኩት“ በማለት ምክሩን ያክላል።

ነቢይ ኢያሱ እስራኤልን “መነሃ ታመልኩ-ማንን ታመልካላችሁ? ፤ ወአንሰ ወቤትየ እግዚአብሔርሃ ናመልክ እስመ ቅዱስ ውእቱ- እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ እርሱ ቅዱስ ነውና“ ብሎ ጠይቋቸው ነበር። “ወይቤልዎ ሕዝብ ለኢያሱ እግዚአብሔር አምላክነ ናመልኮ ወቃለ እግዚአሁ ንሰምዕ- ሕዝቡም ኢያሱን ፈጣሪያችን እግዚአብሔርን እናመልካለን የእርሱንም ቃል እንሰማለን አሉት“ ይላል። ኢያ ፳፬፥፲፬ ለእስራኤል ይህ ባዕዳን አማልክትን ክዶ እግዚአብሔርን በማመን ለመጽናት ቃል መገባባታቸው ጸንተውም መገኘታቸው አባቶቻቸው በበረሀ ሳሉ ካገኛቸው መከራ ሁሉ ድነው የተስፋይቱን ምድር በሰላምና በብዙ በረከት እንዲኖሩበት ረድቷቸዋል።

ወገኖቼ ሃይማኖት ሀብትም፣ ጋሻም፣ ዕውቀትም ነው፤ በሃይማኖት በዚህ ዓለም የማይቻል የሚመስለውን ሁሉ ድንቅ ነገር ማድረግ ይቻላል ጌታችን በወንጌል “ለእመ ብክሙ ሃይማኖት መጠነ ሕጠተ ሰናፔ ኵሉ ይትገበር ለክሙ – የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል ሃይማኖት ቢኖራችሁ ሁሉን ማድረግ ይቻላችኋል“ ሲል በሃይማኖት የሚገኝን ጸጋና ክብር ኃይልና ክኂሎት እንዳለ። ማቴ ፲፯፥፲፱ ከሃይማኖት ስንርቅ ይህ ሁሉ ኃይላን ችሎታ ክብርና ጸጋ ከእኛ እንደራቀ ልናስተውል ይገባል። በእኛ ትውልድ ሥራ የሚጀምር እንጂ የሚፈጽም፤ የሚዘራ እንጂ ምርቱን አፍሶ በልፋቱ ዋጋ ደስ የሚሰኝ ቡሩክ ብእሲ እምብዛም አልገኝ ያለበት፤ በረከት ከሰው ልጆች የራቀው፤ ደኃና ሀብታም እኩል የሚጨነቅበት፤ ጉልበት ያለውና ምስኪኑ አኩል የሚሰጋበት ምክንያቱ ሌላ ሊሆን አይችልም ሰው ከሃይማኖት ሰው ከፈጣሪው በመራቁ ምክንያት አዳኙ ሰይጣን ሠልጥኖበት ተበረ ታቶበት ነው። ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር እመኑ ብላ ማስተማሯ አምልኮተ እግዚአብሔር ከገጸ ምድር ጠፍቶ እግዚአብሔር ይጎዳል ብላ ሰግታ አይደለም። አምልኮተ እግዚአብሔር በዘመነ አበውና በብሉይ ኪዳን ነበር፤ ዛሬም በሐዲስ ኪዳን አለ፤ ወደፊትም እስከዓለም ፍጻሜ ይኖራል እርሱ ባወቀ ወዳጆቹ ያመልኩታል። ሰው እግዚአብሔርን አለ ብሎ ቢያምን ይልቁንስ የሚጠቀመው እርሱ ነበር። አሁንም ሰዎች ከመጻሕፍት ብቻ ያይደለ ከመከራችን ተምረን ወደ ሃይማኖት ልንመለስ ዓለማትን ፈጥሮ ወደሚገዛ አምላክ ፊታችንን ልንመልስ ልባችንንም ልናስገዛ ይገባናል። ያን ጊዜ መቅሠፍት ይወገዳል ቸነፈር ይገሠጻል። ያን ጊዜ ፍትሕና ሰላም ይሰፍናል፤ ድኆች ጠግበው ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፤ ባለጸጎች ያለ ስጋት ይውላሉ፤ መሪና ተመሪ አሳዳሪና ተዳዳሪ ተስማምተውና ተረዳድተው ይኖራሉ። ያን ጊዜ የድል አድራጊው የክርስቶስ ኢየሱስ ወዳጆች ድል አድራጊዎች እንሆናለን፤ የአዳኙ ጠላታችን ወጥመድ ይሰባበራል።

አምላከ ኃይል እግዚአብሔር በረድኤቱ ይጎብኘን በከኃሊነቱ ከመከራ ሁሉ ይጠብቀን፤ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን በቸርነቱ ይጠብቅልን፤ እግዚአብሔር ይባርካችሁ የድንግል ማርያም በረከት አይለያችሁ።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *