በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የምሥራቅ፣ ምዕራብ እና ደቡብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የ፳፻፰ ዓ/ም የሥራና አገልግሎት ክንውን ዘገባ

የደ/ም/ም አውሮፓ ሀገረ ስብከት በ2008 ዓ/ም የሥራ ዘመን በዓመቱ መጀመሪያ ላይ በምልዐተ ጉባዔ በጸደቀው የሥራ ዕቅድ መሠረት ለሀገረ ስብከቱና በሥሩ ለሚገኙ አድባራት ሥራና አገልግሎት መጠናከር አልፎ ተርፎም ለመላይቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መስፋፋት አስተዋጽኦ ያላቸው ተግባራትን ለማከናወን በ2007 የሥራ ዘመን ካደረገው ባልተናነሰ መልኩ ያላሳለሰ ጥረት አድርጓል።

ምንም እንኳ በአንዳንድ አድባራት ድንገት የሚከሠቱ አለመግባባቶችና አለመግባባቶቹን ለመፍታት ወይም አጣርቶ ተገቢውን አስተዳደራዊ ውሳኔ ለመስጠት የሚደረገው ሰፊ አቅምና ጊዜ የሚጠይቅ የሥራ ሂደት በዕቅድ የተያዙ ተግባራትን በታቀደው መሠረት ለመፈጸምና ለማስፈጸም የራሳቸው የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው ባይቀርም በረድኤተ እግዚአብሔር ለቤተ ክስርቲያን አንድነት፣ ሰላምና ብልጽግና የቀና አመለካከትና ቁርጥ ዓላማ ካላቸው የሀ/ስከቱ አስተዳዳር አባላት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ምእመናንና የሰ/ት/ቤት አባላት እገዛና ተባባሪነት ጋር ቀላል ግምት የማይሰጣቸውና ለቀጣይ የሥራ ጊዜ ምቹ ሁኔታዎችን ያስገኙ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል። ጥቂቶቹን እንደሚከተለው እናቀርባለን።

1.ሀገረ ስብከቱን የሀገሪቱ ሕግ በሚጠይቀው መልኩ በማኅበርነት ለማስመዝገብ የተጀመረውን ሕገ ደንብ የማዘጋጀትና የማጸደቅ እንቅስቃሴ በትኩረት በመከታተል ሕገ ደንቡ ከአጽዳቂው መንግሥታዊ መ/ቤት በተሠጡ የማስተካከያ አስተያየቶች መሠረት ተገቢው ማሻሻያ ተደርጎበት ለዕውቅና ሰጪው ፍ/ቤት የቀረበ ሲሆን በሳምንታት ዕድሜ ውስጥ አጽድቆ ማስረጃ ለመስጠት የአጭር ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶናል።
2. ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ መርሐ ግብሮችን ነድፎ በመተግበር የሀ/ስከቱ መሠረታዊ ችግር የሆነውን የገንዘብ እጥረት በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ ታስቦ የሀ/ስከቱ የል/ሰ/ጉ/ማ/መ እና የሂሣብ መምሪያ ኃላፊዎች የሚመሩት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር አዘጋጅ ጊዜያዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ የትምህርት ጉባኤ፣መጽሔት፣የቀን መቁጠሪያ፣ ሎተሪና የቃል ኪዳን ሰነድ የተካተቱበት መርሐ ግብር ተዘጋጅቷል። ሁሉንም የሀ/ስከቱ አካባቢዎች የሚያዳርስ በቂ ቅስቀሳ ማድረግ ባለመቻሉና አንዳንድ አድባራትም ምንም ዓይነት ተሳትፎ ለማድረግ ፈቃደኝነት ባለማሳየታቸው የተገኘው ውጤት ከዕቅዱ አንጻር አመርቂ ነው ባይባልም ከ8 ሺህ ኦይሮ በላይ ገቢ በማስገኘት የሀ/ስከቱን ዕለታዊ ወጪዎች ለመሸፈን የማይናቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
3. ትምህርተ ወንጌልን ከማስፋፋትና ወቅታዊ መጃዎችን ለምእመናን ከማቅረብ ጋር በተያያዘ በየዓመቱ አንድ ጊዜ እንዲታተምና በመላ የሀ/ስከቱ አካባቢዎች እንዲሠራጭ ታስቦ በ2008 ዓ/ም የተጀመረው “ኤፍራታ“ የተሰኘው መጽሔት ቁጥር ፩ ሙሉ በሙሉ የተሠራጨ ሲሆን ከ2009 ዓ/ም አዲስ ዓመት ጋር ተያይዞ እንደሚሠራጭ የሚጠበቀው ቁጥር ፪ ጥራቱንና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተዘጋጅቶ ቀርቧል። የዘመን መቁጠሪያም በተመሳሳይ መልኩ ታትሞ በሥርጭት ላይ ይገኛል። በሀ/ስከቱ ድረ ገጽም አጽዋማትንና በዓላትን ምክንያት በማድረግ የብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ቃለ ምዕዳንና ሌሎች ትምህርታዊ ጽሑፎች መልእክቶች ተላልፈዋል። ሀገራዊና መላ ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከቱ ክሥተቶችንና የሥራ ሁኔታዎችን የሚገልጹ መረጃዎችም ተላልፈዋል።
4. ቤተ ክርስቲያን ባልተተከለባቸው አካባቢዎች በጽዋ ማኅበር ስም የሚሰባሰቡ የቤተ ክርስቲያን አባላትን መዝግቦ ለመያዝና በጥንቃቄ እንዲያድጉ ለማድረግ በተደረገ ጥረት በዓመቱ የዕውቅና ጥያቄ ላቀረቡ 4 የጽዋ ማኅበራት አስፈላጊው ማጣራትና ክትትል ከተደረገ በኋላ ዕውቅና የተሰጣቸው ሲሆን 3ቱ ወደ ቤ/ክንነት ለማደግ የሚጠየቁትን መስፈርቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ በማሟላታቸው ታቦተ ሕግ ገብቶላቸው ወደ አጥቢያ ቤ/ክንነት አድገዋል። 4ኛውም የጽዋ ማኅበር ወደ ቤ/ክንነት የሚያሳድገውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ሲሆን ወርኃዊ ጉባዔዎች ከሀ/ስከቱ በሚመደቡ ካህናትና ሰባክያን መሪነት በአግባቡ እየተካሄዱ ናቸው። ወደ አጥቢያ ቤ/ክንነት ያደጉት የክሮንበርግ ቅዱስ ዑራኤል እና የዱሰልዶርፍ አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ አ/ክናት ጀርመን እና የዑድኒ አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ ቤ/ክ ጣልያን ሲሆኑ በሂደት ላይ ያለው የጽዋ ማኅበር የብሬመን ቅዱስ እስጢፋኖስ ጽዋ ማኅበር ነው።
5. በሀገራችን በኢትዮጵያ ከድርቅ ጋር በተያያዘ በተከሠተው የረሀብ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች መርጃ የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ ሠርኩላር ተላልፎ ብዙ አድባራት ጥሪውን በመቀበል ጸሎተ ምሕላ ያደረሱና የርዳታ ገንዘብ አሰባስበው ወደ ሀ/ስከቱ ያስተላለፉ ሲሆን ከ10 አድባራት የተሰበሰበው 16,662,40 /አስራ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስድሳ ሁለት ኦይሮ ከአርባ ሳንቲም/ ከሪፖርት ጋር ቅዱስ ሲኖዶስ ላቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ በባንክ ተላልፏል።
6. የውጭ ግንኙነትን ለማጠናከር በሥራ ዘመኑ የተሻለ እንቅስቃሴ ተደርጓል። ልምድ ለመለዋወጥና በጋራ ጉዳይ ላይ ለመተባበር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመመካከር ተቀማጭነታቸው በጀርመን ሀገር ከሆነ ከሶርያ፣ ከግብጽ እና ከግሪክ ኦርቶዶክስ አ/ክናት ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን ሊቃነ ጳጳሳቱና ረዳቶቻቸው በቀጣይ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ለአ/ክናት በሚሰጠው መብት ሁሉንም አ/ክናት ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል የጋራ ፕሮግራም ነድፎ ከሀ/ስከቱ ጋር በጋራ ለመሥራት ፈቃደኝነታቸውን አረጋግጠዋል። ከዚሁም ጋር በተያያዘ ለቤተ ክርስቲያናችን ልዩ አክብሮት ያላቸውና ሀ/ስከቱን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በገንዘብና በምክር በመደገፍ ላይ የሚገኙት የግብጹ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አንባ ዳምያን በሀ/ስከቱ ግብዣ በታኅሣስ ወር 2008 ዓ/ም ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ ቅዱሳት መካናትን ጎብኝተዋል፤ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክም ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል። ብፁዕነታቸው በጉብኝታቸው ወቅት ባዩትና በተደረገላቸው ፍቅር የተሞላበት አቀባበል በእጅጉ መርካታቸውን የገለጹ ሲሆን ወደፊትም በተለይ የርዳታ ጥያቄ ላቀረበላቸው አንድ ጥንታዊና ታሪካዊ ደብር ሙዚየም ለማሠራት ቃል ገብተዋል።
7. ለሀ/ስከታችን ቀና ትብብር በማድረግ የሚታወቀውና ብዙ ኢትዮጵያውያን ምእመናን በአጽዋማት ጊዜ ሱባዔ የሚይዙበት የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ የቅዱስ እንጦንስ ገዳም በእንግዶች ማረፊያ አድባራሽ ላይ ከ3 መቶ ሺህ ኦይሮ በላይ የሚገመት ንብረት ያወደመ የእሳት ቃጠሎ አደጋ የደረሰ ሲሆን ቤ/ክኒቱ ለቤ/ክናችንና ለምእመናን እያደረገችው ካለው እኅታዊ ትብብር አንጻር አጋርነትን መግለጽ እንደሚገባ በማመን የ1,500,00 /አንድ ሺህ አምስት መቶ ኦይሮ/ ድጋፍ ተደርጓል። ከተለገሰው ገንዘብ ላይ 1 ሺህ ኦይሮ (2/3 ኛው) ከማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ቅርንጫፍ የተገኘ ነው።
8. “ዝክረ ቅዱስ ያሬድ“ በሚል ስያሜ የቅዱስ ያሬድን ታሪክና ሥራ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያንን ትውፊትና ሥርዓት የሚያስተዋውቅ ዓመታዊ ዐውደ ጥናትና ጉባዔ በዓመት አንድ ጊዜ በግንቦት ወር በሀገረ ስብከት ደረጃ በሁሉም አድባራት በተራ ለማክበር ታቅዶ በ2008 ዓ/ም የመጀመሪያው ዙር በዓል በካ/ም/ቅ አቡነ ተክለሃይማኖት ቤ/ክ (ጀርመን) በታላቅ ድምቀት ተከብሯል። በበዓሉ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናትና ቁጥራቸው በርከት ያለ ምእመናን የተገኙ ሲሆን ተጋባዥ ምሁራን በተለያዩ አርእስት ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርበዋል። በዓይነቱ ለየት ባለ መልኩ የተከበረው ይህ በዓል ታዳሚዎችን ከማርካቱ በተጨማሪ ታሪክንና ባህልን ከማስተዋወቅ አንጻር ካለው ሀገራዊ ፋይዳ በመነሣት ትልቅ ግምት የሰጠው የዶቸቬለ ሬድዮ ጣቢያ በቂ የአየር ሽፋን ሰጥቶ ዘግቦታል፤ የከተማው ጋዜጣም ተመሳሳይ ዘገባ ከአድናቆት ጋር አውጥቷል።
9. ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቤ/ክናችንን ታሪክ፣ መሠረተ እምነት፣ ትውፊትና ሥርዓተ አምልኮ ወጥ በሆነ መልኩ ለማስተዋወቅ በተጨማሪም በአውሮፓ ተወልደው ለሚያድጉ ወጣቶችና ታዳጊዎች ማስተማርያነት እንዲያገለግል ለማድረግ በማሰብ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጭር የሃይማኖት፣ የታሪክና የሥርዓት መግለጫ“ የሚለውን በቅዱስ ሲኖዶስ የታተመች አነስተኛ መጽሐፍ ወደ ጀርመንኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለአገልግሎት መስጫነት ብቻ ተባዝቶ ጀርመንኛ ቋንቋ በሚነገርባቸው በጀርመንና በስዊዘርላንድ ላሉ አድባራት እንዲከፋፈል ጥረት እየተደረገ ይገኛል። የአማርኛ ለቀማ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን የትርጉም ሥራው በመሠራት ላይ ይገኛል። አጠቃላይ ሥራው በቀጣይ 3 ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይታመናል። ወደ ፈረንሳይኛ፣ ጣልያንኛ እና ግሪክኛ የመመለሱም ሂደት ደረጃ በደረጃ የሚከናወን ይሆናል።
10. አድባራት ስብከተ ወንጌልንና ሰ/ት/ቤቶችን ለማስፋፋትና ለማጠናከር የሚያስችል አቅም እንዲያጎለብቱ የሚያግዙ አገልጋዮችን ለማፍራት በማሰብ የ3 ወር ተከታታይ ሥልጠና በቀጥታ ሥርጭት ለመስጠት ታቅዶ የመጀመሪያው ዙር ሥልጠና በነሐሴ ወር 2008 ዓ/ም ተጀምሯል። ከተለያዩ አድባራት የተውጣጡ 21 ሠልጣኞች ሥልጠናውን እየተከታተሉ ይገኛሉ። ሥልጠናው ሲጠናቀቅ ሥልጠናውን በአግባቡ የተከታተሉ ሠልጣኞች የምስክር ወረቀት የሚሰጣቸው ሲሆን በሥልጠናው ፍጻሜ በየደብራቸው መርሐ ግብር በመምራትና ሰ/ት/ቤቶችን በማጠናከር እንዲያገለግሉ ይደረጋል። ሥልጠናው ቀጣይነት ያለው ሲሆን ሥልጠናውን በመስጠት የሚያገለግሉት መምህራን በቤ/ክ የታወቁና በቂ የማሠልጠን ችሎታ ያላቸው የአድባራት አስተዳዳሪዎችና ሰባክያን ናቸው።
11. ወደ ቤ/ክህነት የሚደረግን የገንዘብ ፈሰስ በተመለከተ ምንም እንኳ ሀ/ስከቱ ከመንበረ ጵጵስና ቤት ኪራይ እምብዛም ያለፈ ገቢ የሌለውና አድባራት በከፊል ዓመታዊ አስተዋጽኦዋቸውን የማይከፍሉ በመሆናቸው ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት ያለበት ከመሆኑ የተነሣ ብዙ እንቅስቃሴዎች የሚከናወኑትም ሆነ አስፈላጊ ነገሮች የሚሟሉት በግለሰቦች ድጋፍ ቢሆንም የቤ/ክኒቱን ሕግ አክብሮ መሥራት ለውይይት የማይቀርብ ግዴታ በመሆኑ በ2008 ዓ/ም ለመጀመሪያ ጊዜ ከነበረው አነስተኛ ገንዘብ ላይ 1,000,00/አንድ ሺህ/ ኦይሮ ፈሰስ ያደረገ ሲሆን በ2008 ዓ/ም በ2 እጥፍ በማሳደግ 3,000,00 /ሦስት ሺህ/ ኦይሮ እንዲከፈል ተደርጓል።
12. ቤተ ክርስቲያናችን አዳዲስ ጳጳሳትን ለመሾም በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል እየተደረገ ባለው የዕጩዎች ምልመላ ውስጥ እንዲሳተፉ በሀ/ስከቱ ውስጥ ከ4 ዓመታት በላይ በደብር አስተዳዳሪነት በማገልገል ላይ ካሉት ቆሞሳት መካከል 5 አባቶችን በዕጩነት እንዲመዘገቡለት ያቀረበ ሲሆን ለመጨረሻ ዙር ደረሱ ከተባሉ ጥቂት አባቶች 3ቱ ሀ/ስከታችን ካቀረባቸው ዕጩዎች መካከል ናቸው። ይህም ለሀ/ስከቱም ሆነ በሀ/ስከቱ ውስጥ ለሚገኙ ካህናትና ምእመናን ታላቅ ደስታና ክብር ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ በዓመቱ ውስጥ ለቅስና ማዕረግ የሚያበቃ አገልግሎትና ትምህርት ያለው 1 ዲያቆን የቅስና እንዲሁም ለዲቁና የሚያበቃ ትምህርት የተከታተሉ 5 ደቀመዛሙርት የዲቁና ማዕረግ ከሀ/ስከቱ ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋል።
13. የሀገረ ስብከቱ አንድ የሥራ ክፍል ሆኖ በመሥራት ላይ ባለው የማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል በዓመቱ ውስጥ በርካታ የትምህርት ጉባዔያት በሀ/ስከቱ ጽ/ቤት ፈቃድ ከአድባራት ጋር በመተባበር አዘጋጅቷል በርካታ ምእመናንም ጉባዔያቱንና በተጓዳኝ በሀገር ቤት ያሉና ድጋፍ የሚያሻቸውን ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ት/ቤቶች ወቅታዊ ሁኔታ ለማስተዋወቅ የተዘጋጁ ዐውደ ርእዮችን በንቃት ተሳትፈዋል። ሐዊረ ፍኖት የተሰኘውንም ዓመታዊ ጉባዔ አዘጋጅቷል።

ሥራ ዘመኑ ያጋጠሙ ችግሮች
1. እንዳለፉት የሥራ ዘመናት ሁሉ የጥቂት አድባራት በወቅቱ የተወሰኑ አድባራት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ዓመታዊ የገንዘብ አስተዋጽኦ አለመክፈል ሀ/ስከቱ በገንዘብ እጥረት ምክንያት እንቅስቃሴው እንዲገደብ ካደረጉ መሠረታዊ ችግሮች አንዱ ነው። ሀ/ስከቱ ሌላ የገንዘብ ምንጭ ሊኖረው ስለማይችል አድባራቱ መንፈሳዊ ግዴታ መሆኑን ዐውቀው የተጣለባቸውን አነስተኛ የገንዘብ አስተዋጽኦ በወቅቱ እንዲከፍሉ ሊደረግ በማይከፍሉትም ላይ አስተዳደራዊ ርምጃ ሊወሰድ ይገባል።
2. ጥቂት አድባራት ከሀ/ስከቱ ጋር አብሮ ለመሥራት ሙሉ ፈቃደኝነት አለማሳየታቸውና የሚተላለፉላቸውን መመሪያዎችና መልእክቶች በአግባቡ ለሕዝብ እንዲደርሱና ተፈጻሚነት እንዲያገኙ አለማድረጋቸው በርካታ ተግባራት በታቀዱት መሠረት እንዳይተገበሩ ውጤታቸውም ከግምት በታች እንዲሆን ሚና ተጫውቷል። ይህም መፍትሔ የሚያሻው ዐቢይ ችግር በመሆኑ ከአድባራቱ ኃላፊዎች ጋር ግልጽ ውይይት ተደርጎ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል።
3. አድባራት እንግዳ መጋበዝ ሲፈልጉ ፈቃድ እንዲጠይቁ በመደረጉና ብዙዎች አድባራት በዚሁ መሠረት በመሥራታቸው የተጋባዥ ሰባክያንና ካህናትን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የተቻለ ቢሆንም በግልሰቦች እየተጋበዙ የሚመጡትን ማስቆም ስለማይቻል በቤ/ክን ያላቸውን የአገልግሎት ኃላፊነት በማስረጃ ማሳየት የማይችሉ ካህናት እንደሆኑ የሚናገሩ ሰዎች መጥተዋል። ባሕታዊ ነኝ አጠምቃለሁ ያሉትን በርግጥ በአየር መግለጫ በመስጠት እንቅስቃሴያቸው እንዲከሽፍ ተደርጓል፤ ንስሓ ልጄ ጋበዘኝ የሚሉትን ግን መድረክ ቢከለከልም በማኅበር በሰፈር ሲመችም በአንዳንድ ቦታዎች ትንንሽ ክፍተቶችን በመጠቀም የተዛባ ትምህርት አስጨብጠው መሄዳቸው አልቀረም። የተዛባውንም አመለካከት መልሶ ለማለዘብ ብዙ ድካም እየጠየቀ ይገኛል። ይህም በሁሉም ወገኖች በተለይም በአድባራት አስተዳዳሪዎች ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።
4. የቪስባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክንን በተመለከተ ሀ/ስከቱ ባላቸው ኃላፊነት ላይ ላልተወሰነ ጊዜ ደርበው በአስተዳዳሪነት እንዲያገለግሉ የመደባቸው መ/ስብሐት ተክሌ ሲራክ ለ1 ዓመት ያህል ሲያገለግሉና ሕጋዊ አሠራር እንዲከተል ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው በመጨረሻ ንብረት ትረከባለህ ተብለው ተጠርተው እርሳቸው እንዳይገኙ በተደረገበትና የወረዳ ቤ/ክህነቱ ኃላፊ በመሩት ስብሰባ ሕዝቡ ተስማማ በተባለው መሠረት ንብረቱን በወረዳ ቤ/ክህነቱ ኃላፊ እጅ እንዲቆይ መደረጉ ስለተነገረኝና ከዚህ በኋላ ደብሩን ላስተዳደር ስለማልችል ሀ/ስከቱ ኃላፊነቱን ያንሣልኝ በማለት ራሳቸውን ከኃላፊነት አግልለዋል። ምንም እንኳን ሂደቱ ሕግ የጣሰና ኀዘን ላይ የሚጥል ቢሆንም በተጨማሪም በአንድ ጎን የምእመናን አቤቱታ በተደጋጋሚ መቅረቡ በሌላ በኩል ርክክቡን እንዲያስፈጽም ኃላፊነት የተሰጠው የወረዳ ቤ/ክህነቱ ለወራት የደረሰበትን ሳያሳውቅ መዘግየቱ ሀ/ስከቱን ቢያሳስበውም ኃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ የያዘ አካል በመኖሩ (የጀርመን ወረዳ ቤ/ክህ) ለጊዜው ምንም ዓይነት ውሳኔ ከመስጠት ታቅቦ ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
5. በሠራ ዘመኑ የውስጥ አለመግባባት ከተከሠተባቸው አድባራት መካከል ከፍተኛ ግምት የተሰጠው አለመግባባት የተከሠተው በአቴንስ ም/ደ ኪዳነምሕረት ቤ/ክ (ግሪክ) ነው። ሀ/ስከቱ ልዑካንን በመላክ በእርቅ የሚፈቱ ጉዳዮች በእርቅ እንዲፈቱ አስተዳደራዊ ዳኝነት ለሚያሻቸውም ጉዳዮች አስተዳደራዊ ውሳኔ በመስጠት አለመግባብቱ እንዲከስም አድርጓል። ይሁን እንጂ አሁንም ተመሳሳይ አለመግባባት መኖሩን በተጨባጭ የሚያሳይ አቤቱታ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የቀረበ ሲሆን የአቤቱታው ግልባጭ ለሀ/ስከቱ ጽ/ቤት ደርሷል። ጉዳዩ ወደ በላይ አካል አልፎ በመሄዱና በመሀል አቋርጦ መግባቱ አግባብ ባለመሆኑ ሀገረ ስብከቱ የቅዱስነታቸውን አባታዊ መመሪያ ወይም ውሳኔ ጠብቆ ተፈጻሚ ያደርጋል።
6. “በሙኒክ ከተማ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የቅዱስ አማኑኤል ቤ/ክ“ በሚል ስያሜ ቤ/ክ ሊከፈት ነው፤ የሀ/ስከቱ ሊቀ ጳጳስና የወረዳው ኃላፊ ፈቃድ ሰጥተዋል የሚል አሰተኛ መግለጫ አየር ላይ በማዋል የሚንቀሳቀስ ቡድን በሐምሌ ወር 2008 ዓ/ም አጋጥሟል። የሙኒክ ደ/ብ/ቅ ገብርኤል ቤ/ክ ጉዳዩን በወቅቱ በማስታወቁና ቡድኑ የሚያወጣቸውም መግለጫዎች ለሀ/ስከቱ በመድረሳቸው ሀ/ስከቱ እንቅስቃሴው የማይታወቅና ያልተፈቀደ ከሕገ ቤ/ክንም አንጻር የማያስኬድ መሆኑ ተገልጾ ምእመናን በማንኛውም መንገድ ከመተባበር እንዲቆጠቡ የሚያሳስብ መግለጫ በድረ ገጹ ሰጥቷል። ከመግለጫው ወዲህ ቡዱኑ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አላደረገም።

የ2009 ዓ/ም የሥራ ዕቅድ
ሀገረ ስብከቱ በ2009 ዓ/ም የሥራ ዘመን ሊያከናውናቸው ካቀዳቸው ተግባራት መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦
1.. ትምህርተ ሃይማኖትን ከማስፋፋት፣ ቤ/ክንን ከማስተዋወቅና ተተኪ ካማፍራት ጋር በተያያዘ በ2008 ዓ/ም የተጀመሩትን የመጽሐፍ ትርጉምና ሥርጭት ሥራ፣ የተከታታይ ትምህርት ሥልጠና፣ የድረ ገጽ ትምህርታዊ መግለጫዎችና መልእክቶችን የማስተላለፍ መርሐ ግብሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግ፤
2. ምእመናን ቅዱሳት መካናትንና ታሪካዊ ቦታዎችን በመጎብኘት ስለ ሃይማኖታቸው ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሰፉ ለማገዝ እግረመንገዱንም ክርስቲያናዊ አንድነትን ለማጠናከር በዓመቱ ውስጥ 2 መንፈሳዊ ጉዞዎችን ወደ ግሪክና ወደ ቱርክ ማድረግ፤
3. የተጀመረውን ለሀ/ስከቱ ማዕከል መሆን የሚችል ቋሚ ቦታ የማፈላለግ እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠል፤
4. የተጀመረውን “ዝክረ ቅዱስ ያሬድ“ ዓመታዊ በዓል በተመሳሳይ ሁኔታ በተረኛ ደብር በታላቅ ድምቀት ማክበር፤
5. ሀ/ስከቱን ለማቋቋም የሚረዳ የገንዘብ ገቢ ማስገኘት የሚችል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ለአንድ ጊዜ ማዘጋጀት፤
6. ቤተ ክርስቲያን ባልተተከለባቸው አካባቢችና በስደተኛ ጣቢያዎች የሚገኙ ምእመናንን በማስባሰብ በአቅራቢያቸው ከሚገኙ አ/ክናት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት፣ በሰ/ት/ቤትነት ወይም በጽዋ ማኅበርነት ማደራጀት፤
7. ቤተ ክርስቲያናችንን ተጠቃሚ በሚያደርግ ደረጃ ከአኃት አ/ክናት ጋር የተጀመሩ ግንኙነቶችን አጠናክሮ መቀጠል።

ማጠቃለያ፡
ከዚህ በላይ በቅደም ተከተል በቀረበው ዘገባ ማየት እንደሚቻለው ሀገረ ስብከቱ በ2008 ዓ/ም የሥራ ዘመን ምንም እንኳ ሥራን የሚያበላሹ የሠራተኛንም ሞራል የሚያኮላሹ ሰው ሠራሽ እንቅፋቶች ቢያጋጥሙትም በርካታ ጠቃሚ ተግባራትን ማከናወን ችሏል። የሥራ ውጤቱ በገንዘብ ባይተመንና በፐርንሰት ባይሰላም ከምንም ተነሥቶ ከእግዚአብሔር አጋዥነት ጋር በጥቂት ተባባሪዎች አድባራት፣ ካህናት እና ምእመናን ድጋፍ ብቻ የተገኘ ውጤት በመሆኑ የሚያስጀምርና የሚያስፈጽም እግዚአብሔርን በእጅጉ እንድናመሰግን ግድ ይለናል። በዚህ አጋጣሚ ከዚህ በላይ ለተገለጹት ተግባራት መከናወን በማንኛውም መልኩ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን በሙሉ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም ልናመሰግን እንወዳለን። በቀጣይ የሥራ ዘመንም ቢቻል የተሻለ ያም ባይሆን የተመጣጠነ የሥራ ፍሬ ለማሳየት የሁሉም ወገን ድጋፍ እንዳይለየን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

ፍርቃን ለአምላክነ

የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት

ነሐሴ 2008 ዓ/ም ጀርመን

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *