በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የምሥራቅ፣ ምዕራብና ደቡብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የ፳፻፯ ዓ/ም የሥራና አገልግሎት ዘመን ዓመታዊ ሪፖርት

ሀገረ ስብከቱ በአዲስ መልክ ተዋቅሮ ሥራውን ከጀመረ ወዲህ ፳፻፯ ዓ/ም ፪ኛው የሥራ ዘመን ሲሆን በሥራ ዘመኑ ሀገረ ስብከቱን ከማደራጀት ጎን ለጎን የተቋቋመበትን መንፈሳዊ ተልዕኮ በአግባቡ በመወጣት በሥሩ ለሚያስተዳድራቸው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትናትና ለሕዝበ ክርስቲያኑ አልፎ ተርፎም ለመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት አቅምና ሁኔታ በፈቀደው መጠን የሥራና የአገልግሎት መሰናክል የሆኑ ሁኔታዎችን በብዙ ትዕግሥትና በመንፈሳዊ ጥበብ በማለፍና በማሳለፍ በዓመቱ ሊያከናውናቸውን ያቀዳቸውንና በዕቅድ ውስጥ ባይያዙም አስፈላጊ ሆነው የተገኙ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፤ አበረታች ውጤትም ተገኝቷል።
ከተከናወኑትም ተግባራት መካከል የሚከተሉት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡

1. አድባራት ከአስተዳደር ብልሽት፣ ከገንዘብና ንብረት ብክነት የጸዳና መግባ ባትና መተማመን የሰፈነበት ተመሳሳይ የአስተዳደር ሥራ አፈጻጸም ስልት እንዲከ ተሉ ለማስቻል በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ሥራ ውስጥ ኃላፊነትና ድርሻ ያላቸው የሰ/ጉ አባላት የቃለ ዓውዲ ሕገጋት፣ የአስ ተዳደር ሥራ አፈጻጸምና የሂሣብና ንብረት አያያዝ ሥልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ በታቀደው መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ በጀርመን ለሚገኙ አድባራት የካቲት ፯ ቀን ፳፻፯ ዓ/ም የሙሉ ቀን ሥልጠና በሀ/ስከቱ ጽ/ቤት በተሳካ ሁኔታ የተሰጠ ሲሆን ሥልጠናውን የተከታተሉ ከ፶ በላይ የሚሆኑ የ፱ አ/ክናት ተወካዮች በሥልጠ ናው ጠቃሚ ዕውቀትና ልምድ መቅሰ ማቸውን ገልጸዋል። ተሳታፊዎቹ የሥል ጠናው ማንዋል ታትሞ እንዲሠጣቸው በጠየቁት መሠረትም ታትሞ ለአድባራት በነፃ እንዲታደል የተደረገ ሲሆን ሥል ጠናው በቀጣዩ ዓመትም በሌሎች የሀ/ስከቱ አካባቢዎች ይቀጥላል።

2. ሀ/ስከቱ ምንም እንኳ በቤተ ክርስቲያኒቱ ወሳኔ ሰጭ አካል ፈቃድና ዕውቅና የተቋቋመ ሕጋዊ አካል ቢሆንም በአውሮፓ ሀገሮች ውስጥ በኦፊሲያል ለመንቀሳቀስ፣ ለመደራጀትና አጥቢያዎችንና መሰል ተቋማትን ለማደራጀት በአንድ የአውሮፓ ሀገር በሕጋዊ ማኅበርነት መታወቅና መመዝገብ ስላለበት ማኅበሩን ለማቋቋም የሚያስችል ቃለ ዓዋዲን መሠረት ያደረገ የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና በጀርመንኛ የተዘጋጀ ሲሆን ሕገ ደንቡ በአድባራት አስተዳዳሪዎችና የምእመናን ተወካዮች በተገኙበት ዓመታዊ ጉባዔ ከታየ በኋላ ለሚመለከተው መደበኛ ፍ/ቤት ቀርቦ እንዲ ጸድቅና ሥራ ላይ እንዲውል ይደረጋል።3. ማዕከልን ባልጠበቀ ሁኔታ አድባራት በየራሳቸው የክርስትና ካርድ፣ የጋብቻ ምስክር ወረቀት፣ የሰ/ጉ አባልነት መታወቂያ አትመው የሚጠቀሙበትን ልማድ በማዕከል ደረጃ በሚዘጋጅ አንድ ዓይነትና ወጥ ማስረጃ ወደመጠቀም ለመለወጥ ምንም እንኳ ተገልጋዮች ሰነዶቹ በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ቋንቋ የተዘጋጁ እንዲሆኑላቸው መፈለጋቸው በሀገር ቤት የሚተታመውን ሰነድ ለመጠቀም ባያስ ችልም ይዘቱን እንደጠበቀ በሀገረ ስብከቱ በኩል በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ታትሞ እንዲሠራጭ ማድረግ እንደሚቻልና አንድወጥ ሰነድ መጠቀሙም ፈረጀ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው በማመን የክርስትና ካርድ፣ የጋብቻ ምስክር ወረቀትና የሰ/ጉ አባልነት መታወቂያ ከአማርኛ ጋር በእንግሊዝኛ፣ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ እና ጣልያንኛ በሁለት ቋንቋዎች ታትሞ እንዲሠራጭ ተደርጓል።

4. ወቅታዊ መረጃዎችን ለካህናትና ምእመናን ለማድረስና መልእክቶችን ለማስተላለፍ የምእመናንንም ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተቀብሎ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ሀገረ ስብከቱ ከሕዝበ ክርስቲያን ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጎልበት ያስችል ዘንድ በሀገረ ስብከቱ ስም የፌስቡክ ገጽ(Facebook Page) ተከፍቶ መረጃ የማቀበሉን ተግባር በተሳካ ሁኔታ እያከናወነ ይገኛል። ገጹ የሀገረ ስብከቱን ብቻ ሳይሆን የአድባራትንም የሥራ እንቅስቃሴና መልእ ክቶች እንዲሁም በአጠቃላይ የቤተክ ርስቲያን ጉዳዮች ዙርያ ምእመናን ሊያው ቋቸው ይገባል የሚባሉትን መረጃዎች ሁሉ እያስተላለፈ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስት የገጹ ተመልካች ቁጥር ከ፫ሺህ ፭ መቶ በላይ ደርሷል፤ ምእመናን ገንቢ አስተያየት በመስጠትና ጠቃሚ መረጃዎችን በማቀበል የሚያደርጉት ተሳትፎም አገልግሎቱን በማጠናከርና ትኩረቱንም ትምህርተ ወንጌልን ወደማስፋፋትም በማቅናትየበለጠ ተጠናክሮ እንዲሠራበት የሚያበረታታ ሆኖ ተገኝቷል፤ በዚህ መልኩ ለመቀጠልም የሀገረ ስብከቱ ትምህርት እና የስብከተ ወንጌል መመሪያዎች ተጠናክሮ ለመሥራት ኃላፊነቱን በዋነኛኘት ይወጣሉ።

5. ትምህርተ ወንጌልን ከዓውደ ምሕረት ውጪ በልዩ ልዩ መንገዶች ለማስፋፋት በተያዘው መሪ ዕቅድ መሠረት ለጊዜው በሥራ ዘመኑ “ኤፍራታ“ በሚል ስያሜ በሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ክልሎች ሁሉ የሚሠራጭ መጽሔት አዘጋጅቶ ለማሳተም ታቅዶ የመጽሔት አዘጋጅ ንዑስ ክፍል በማቋቋም እንቅስቃሴ ሲደረግ የቆየ ሲሆን ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጀምሮ በርካታ አባቶች፣ ምሁራንና ሰባክያን አስተማሪ ጽሑፎችን በመጻፍ የተሳተፉበት ቁጥር ፩ ኤፍራታ መጽሔት ታትሞ ለንባብ በቅቷል፤ ከዚህም ጋር የ፳፻፰ ዓ/ም የቀን መቁጠርያ በማዕከል ደረጃ ተዘጋጅቶ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ ተደርጓል።

6. የገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ በተመለከተ በስዊዘርላንድ የሚገኙት ፪ ገለልተኛ አ/ክናት ለተላለፈላቸው ጥሪ ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጡም፤ ከዚሁ በተጨማሪ ከአንዱ ገለልተኛ ቤ/ክ የተገነጠሉ ቡድኖች በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ሌላ ገለልተኛ ቤ/ክ መተከሉን የሚያስታውቅ መልእክት ለሕዝብ ሲያሰራጩ አስተባባሪዎቹን ማግኘት ባይቻልም ሕዝበ ክርስቲያኑ ግን እንዲህ ያለውን ኢቀኖናዊ አካሄድ ከመተባበር ታቅበው በቀኖና ቤ/ክ መሠረት በተተከሉት አ/ክናት ብቻ እንዲገለገሉ በሀ/ስከቱ ፌስ ቡክ ፔጅ መግለጫ ተላልፏል፤ ሙከራቸውም ያልተሳካ ሙከራ ሆኗል። በፍራንክፈርት ጀርመን የሚገኘው ፩ ገለልተኛ ቤ/ክም የዝግጅት ጊዜ ይሰጠን የሚል ደብዳቤ በመላካቸው በትዕግሥት ሲጠበቁ ቢቆዩም እስካሁን ምንም ዓይነት ወደ መዋቅር የመግባት እንቅስቃሴ አላደረጉም፤ ለውይይት ለመቅረብም ፈቃደኝነት አላሳዩም። በመሆኑም የሀ/ስከቱ ጠቅላላ ጉባዔ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲያሳልፍ በአጀንዳነት ቀርቧል።

7. የጻፏቸው ፫ የኑፋቄ መጻሕፍት በሊቃውንት ጉባዔ ከተመረመሩና ኢኦርቶዶክሳውያት መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ ቅዱስ ሲኖዶስ ንስሓ እስካልገቡ ድረስ ከክህነታዊ አገልግሎትና ከማስተማር ያገዳቸው የ () ገዳሙ ደምሳሽ ውሳኔ አፈጻጸም ግለሰቡና ተከታዮቻቸው በፈጠሯቸው አላስፈላጊ ጫናዎች ምክንያት ሲጓተት የቆየና የብዙ ወገኖችን አድካሚ መሥዋዕትነት የጠየቀ ቢሆንም የሀ/ስከቱ ሊቀ ጳጳስ በቦታው ላይ በአካል ተገኝተው ለምእመናኑ ትምህርትና ቡራኬ ከሰጡ ጉዳዩንም በግልጽ ካስረዱ በኋላ ውሳኔ ተቀባዩ በውሳኔው መሠረት ከአገልግሎት እንዲገለሉ ተደርጓል፤ ሀ/ስከቱ በጊዜያዊነት የመደባቸውም መልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ አገልግሎት መስጠትና ደብሩን ማስተዳደር ጀምረዋል። ምንም እንኳ ደብሩ ከ፲ ዓመት በላይ በዓላማ የተሠራውን የጥፋት አካሄድ በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ ለማጽዳትና ግለሰቡ በርቀት ሆነው አሁንም የሚያደርጉትን ተቃራኒ እንቅስቃሴ መቆጣጠር ቀላል የቤት ሥራ ባይሆንም የደብሩ አስተዳደራዊና መንፈሳዊ አገል ግሎት አስተማማኝ ወደሆነ ደረጃ እንዲ መጣ ሀ/ስከቱ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል እየሠራም ይገኛል።

8. ከአስተዳደር አለመግባባት ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል በሮም ደ/ጽ ቅድስት ማርያም ቤ/ክ አስተዳዳሪ መ/ፀ አባ ሰላማ ላይ የተያዘው ጉዳይ ተጣርቶ መፍትሔ እንዲፈለግለት ለማድረግ የአጣሪ ልዑካን ቡድን ተቋቁሞ ለመላክ ቢሞከርም ከደብሩ አስተዳዳሪ ለመተባበር ፈቃደኝነታቸውን የሚያሳይ ምላሽ ባለመገኘቱ ቡድኑ የማጣራት ተግባሩን ማከናወን አልቻለም። ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉዳዩ ወደ መ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት በማለፉ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ከቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ጋር እንዲወያዩበት ተደርጓል። በስዊዘርላንድም ተከሥቶ የነበረውን አለመግባባት አጣሪ ቡድን ልኮ በማጣራት የአለመግባባት መንሥኤዎች ናቸው የተባሉትን በማስተካከል አለመግባባቱን ለማስወገድ ተችሏል። የሀ/ስከቱ ሊቀ ጳጳስም አንድ ጊዜ በጄኔቫ ብቻቸውን አንድ ጊዜ ደግሞ በዙሪክ ከሀ/ስከቱ ዋና ጸሐፊ ጋር በአካል በመገኘት በውይይትና በትምህርት አለመግባባቱ ተወግዶ ሰላምና ስምምነት እንዲሰፍን ጥረት ተደርጓል፤ በአ/ክናቱ አስተዳዳሪ በመ/ገ አባ ኃይለ ጊዮርጊስ እና በምእመናን ተወካዮቹ ቀና ትብብርም ጥረቱ ውጤታማ መሆን ችሏል።

9. በጤና መታወክ ምክንያት ለወራት በጀርመን ሕክምና ሲከታተሉ የቆዩት የግሪክ ም/ደ ኪዳነ ምሕረት ቤ/ክ አስተዳዳሪ ንቡረ እድ ኃይለ ልዑል ወ/ገሪማ የጀመሩት ሕክምና የረጅም ጊዜ ተከታታይ ሕክምና መሆኑ በመታወቁና እርሳቸውም የደብሩ አገልግሎት እንዳይበደል ሀ/ስከቱ አስፈላጊውን እንዲያደርግ ባሳሰቡት መሠረት ከመ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት ፣ ከግሪክ ም/ደ ኪዳነምሕረት እና ከዳርምሽታት ሐ/ኖ ኪዳነ ምሕረት አ/ክናት ጋር በተናጠል በመወያየት ንቡረ እድ ኃይለ ልዑል መላ ዘመናቸውን ቤ/ክንን በትጋት ሲያገለግሉ የኖሩ አንጋፋ አባትና የወንጌል አርበኛ በመሆናቸውና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ የደብሩም አገልግሎት እንዳይበደል የ1 ዓመት ደመወዛቸው ከግሪክ ም/ደ ወደ ዳርምሽታት ሐ/ኖ ኪዳነ ምሕረት ቤ/ክ ፈሰስ እንዲደረግና የዳርምሽታት ሐ/ኖ ኪዳነ ምሕረት ቤ/ክ ሊረዷቸው የሚፈልጉ በጎ አድራጊዎች አሰባስበው ገቢ ማድረግ የጀመሩትን የ1 ዓመት በጀት ጨምሮ ከመጋቢት ፳፫ ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ጀምሮ ለ2 ዓመት በሥራ መድቧቸው እያስተማሩና እየመከሩ ሕክምናቸውን በቅርብ እንዲ ከታተሉ ፤ በምትካቸውም አባ ወ/ሚካኤል ጡዋየ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ መልካም ፈቃድ የግሪክ ም/ደ ኪዳነ ምሕረት ቤ/ክ አስተዳዳሪ ሆነው እንዲ መደቡ ተደርጓል።

10. ከየካቲት ፲፬ እስከ ፲፰ ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ድረስ የሀ/ስከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ እና ሀ/ስከቱ የልማት መምሪያ ኃላፊ ሊቀ ብርሃናት አባ ገ/ሕይወት ፍሥሓ ሀ/ስከቱን በመወከል በጣልያን ሐዋርያዊ ጉዞ ያደረጉ ሲሆን በተያዘው መርሐ ግብር መሠረት በጣልያን ከሚገኙ ፯ አድባራት አስተዳዳሪዎችና የምእመናን ተወካዮች ጋር አገልግሎት ስለማጠናከርና በጋራ ስለመሥራት ውይይት ተደርጓል፤ በሮም ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ሊቀ ጳጳስ ጋርም በአኃትነት መተጋገዝ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጠቃሚ ውይይት ተደርጓል።

11. መንፈሳዊ አገልግሎትን በተመ ለከተ አድባራት እንደየመርሐ ግብራቸው የተለመደ ሳምንታዊ፣ ወርኃዊና ዓመታዊ የአገልግሎት መርሐ ግብሮቻቸውን ያከ ናወኑ ሲሆን በተለይ የካህን እጥረት ጎልቶ የሚታይባቸው ልደት፣ ስቅለትና ትንሣኤን የመሳሰሉ ዐበይት በዓላት መደበኛ ካህን የሌሏቸውን ጨምሮ ካህናትን በማደላደል በሁሉም አ/ክናት አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል። በዓላትም ከሞላ ጎደል ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት ተከብረዋል። በርካታ ሕፃናት ክርስትና ተነሥተዋል፣ ነሳሕያን ለቍርባን በቅተዋል፣ ተጋቢዎች ጋብቻቸውን ፈጽመዋል፤ ለሕሙማንና ለሙታንም ተገቢው ጸሎት ተደርጓል። በዓመቱም በካስል አንዲት ሴት ከነልጇ ከእስልምና ወደክርስትና ተመልሳ ጥምቀተ ክርስትና ተጠምቃለች።

12. ክህነትም በተመለከተ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ በሥራና አገልግሎት ዘመኑ በጀርመን ለ፯ ፣ በስዊዘርላንድ ለ፩፣ በፈረንሳይ ለ፬ እንዲሁም በጣልያን ለ፩ በድምሩ ለ፲፪ ዲያቆናት የቅስና ለ፯ ደቀመዛሙርት ደግሞ የዲቁና መዐርግ ሰጥተዋል።

13. ሚያዚያ ፲፩ ቀን ፳፻፯ ዓ/ም በሊብያ ምድር አይ ኤስ የተባለው አክራሪ እስላማዊ ቡድን በ፳፰ ምእመናን ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ እንዲሁም በየመንና በደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን ግፍ ሕዝበ ክርስቲያንና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እንዲያውቁት፣ ለአደጋ የተጋለጡትንም ወገኖች ለመታደግ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ በሚዲያ ጥሪ የተላለፈ ሲሆን ለሰማዕታቱ ከ፩ ሳምንት በላይ በየደብሩ ጸሎተ ፍትሐት ስለመላው ሕዝበ ክርስቲያንና ስለ ቤተ ክርስቲያን ደኅንነትም ምሕላ ተደርጓል። በዚህ አጋጣሚ ቤተ ክርስቲያኒቱ አጋርነቷን በተግባር ማሳየት መቻሏ የትውልዱ አኩሪ ተግባርና ታሪክ በመሆኑ በመ/ገ አባ ኃይለ ጊዮርጊስ ወ/ማርያም አስተባባሪነት ወደ አራት መቶ ሺህ የኢት. ብር የሚጠጋ ገንዘብ በማሰባሰብ በቤተ ክስርቲያን ስም ለሰማዕታቱ ቤተ ሰቦች ማፅናኛ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ እጅ የገንዘብ ርዳታ እንዲያገኙ ያደረጉትን የስዊዘርላንድን ካህናትና ምእመናን የአድባራቱን አስተዳዳሪ መ/ገ አባ ኃይለጊዮርጊስ ወ/ማርያምን በቅድስት ቤ/ክ ስም ልናመሰግን እንወ ዳለን።

14. በጀርመን ከሚገኙ የግሪክ፣ የግብጽ፣ የሶርያ፣ የአርመን፣ የሩስያ፣ የሕንድ እና የኤርትራ ኦርቶዶክስ አ/ክናት ጋር ከቀኖናና ዶክትሪን ነክ ጉዳዮች ውጪ በጋራ ጉዳይ ላይ ለመተባበርና ለመተጋገዝ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ለማጠናከር የተሞከረ ሲሆን አንዳንዶቹ ለሀገረ ስብከታችን መጠናከር ቀጥተኛ ድጋፍ በማድረግ ሌሎችም በአቅራ ቢያዎቻቸው ከሚገኙ አጥቢያዎቻችን ጋር በመቀራረብ አጋርነታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። በዚህ አጋጣሚ የመንበረ ጵጵስናውን የቤት ኪራይ ክፍያ ላልተወሰነ ጊዜ ለመሸፈን ቃል በገቡት መሠረት ከ፭ ወራት በፊት ጀምሮ ክፍያውን የሚሸፍን የገንዘብ ድጋፍ በየወሩ ወደሀ/ስከቱ የባ.ሒ በማስተላለፍ ላይ የሚገኙትን በጀርመን የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ሊቀ ጳጳስ አንባ ዳምያንን በሀ/ስከቱ ስም ከልብ እናመሰግናለን።

15. ከአብያተ ክርስቲያናት መጠና ከርና መስፋፋት ጋር በተያያዘ በሥራ ዘመኑ በማልታ ፩ በቩርስቡርግ – ጀርመን ፩ በድምሩ ፪ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት (በመድኃኔዓለም እና በቅዱስ ማርቆስ ስም እንደቅደም ተከተላቸው) ከጽዋ ማኅበርነት ወደ ቤተ ክርስቲያንነት እንዲያድጉ የተደረገ ሲሆን አድባራቱ በተጠናከረ ሁኔታ የተሟላ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በተያያዘም በጀርመን ፬ በማልታ ፩ በድምሩ ፭ አድባራት ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ በአካል ተገኝተው ከጎበኙና አደረጃጀታቸውን ከተገነዘቡ በኋላ የቦታ ስያሜ ሲሰጣቸው ለአስተዳዳሪዎቹም የማዕረግ ስያሜ ተሰጥቷል። ተመሳሳይ ጥያቄ እየጠየቁ ያሉ ፬ የጽዋ ማኅበራትም ጉዳይ ጥያቄያቸው በወረዳ ቤ/ክህነቶችና በካህናት አስተዳደር መምሪያ በኩል ከተጠና በኋላ አስፈላጊነቱ ሲታመንበት በውሳኔ ወደ ቤ/ክንነት እንዲያድጉ ይደረጋል።

16. የራስ የሆነ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለመግዛትና ለመገንባት እንቅስቃሴ እያደረጉ ላሉ አድባራት ሀ/ስከቱ ገና በመደራጀት ላይ ያለ በመሆኑ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ባይችልም አድባራቱ እንስቃሴ ያቸውን አጠናክሮ በመቀጠል ዓላማቸውን እንዲያሳኩ የበኩሉን አስተዳዳራዊ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ለ፩ ደብር በሀ/ስከቱ አስተዳደራዊ ክልል ውስጥ ተዘዋውሮ ርዳታ ለማሰባሰብ የሚያስችል የ፪ ዓመት ፈቃድ የሰጠ ሲሆን ተመሳሳይ ጥያቄ ያላቸውን ሌሎች አድባራት በማስተናገድ ላይ ነው። በዚህ አጋጣሚ በአጭር ጊዜ እንቅስቃሴ የራስ የሆነ ሕንፃ ቤ/ክ ገዝቶ ለማስመረቅ የበቃውን የበርሊን ደ/ገ አማኑኤል ቤ/ክንን አስተዳደሪ፣ የሰ/ጉ እና
የሕንፃ ቤ/ክ ግዢ ኮሚቴ አባላት፣ የአጥቢያውን ምእመናን እንዲሁም ዓላማውን በመደገፍ የወር ደመወዛቸውን በጊዜ ገደብ በመክፈል አኩሪ ድጋፍ ያደረጉትን በመላው ጀርመን የሚገኙ ካህናትና ምእመናን የኢትዮጵያ ቤ/ክ በአውሮፓ የራሷ የሆነ ርስተ ምድር እንዲኖራት በማድረግ ታሪክ የማይረሳው ታላቅ የበረከት ሥራ እንዲሠራ ምክንያትና ድንቆችን የሚያደርግ የአምላክ መልእክተ ኞች በመሆናቸው በመላዋ ኦርቶዶክሳዊት ቤ/ክንና በሕዝበ ክርስቲያኑ ስም ልናመሰ ግናቸው እንወዳለን። በቀጣዩም የሥራ ዘመን ቢያንስ በ፩ ወይም በ፪ ደብር /አድባራት/ ተመሳሳይ ታሪክ ይፈጸማል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤ ለዚህም ሀ/ስከቱ ከአድባራት ጋር በመቆም ጠንክሮ ይሠራል።

17. በተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮች ውስጥ የራሳቸው የሆነ ገዳማት ማቋቋም እንደቻሉ አኃት አ/ክናት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ስም የአገልግሎትና የትምህርት ማዕከል ሊሆን የሚችል ገዳም ለማቋቋም ታስቦ በጀርመን ከሚገኙት የካቶሊካዊት እና የወንጌላውያን አ/ክናት ጋር የተዘጋ ገዳም ወይም ቤ/ክ በስጦታ ማግኘት ስለሚቻልበት ሁኔታ እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን ከ1 የካቶሊካዊት ቤ/ክ ሊቀ ጳጳስ፣ ከ1 ንጉሣውያን ቤተሰብ እና ከ1 የከተማ ከንቲባ ተስፋ ሰጭ ምላሽ ተገኝቷል። ራእዩ እውን እስኪሆን ድረስም እንቅስቃሴው ተጠናክሮ ይቀጥላል።

18. የሀ/ስከቱን እንቅስቃሴ ለምእመናን ለማስተዋወቅ፣ ትምህርተ ወንጌልና በልዩ ልዩ አርእስተ ጉዳዮች ላይ ዕውቀት የሚያስ ጨብጡ ጥናታዊ ጽሑፎች ለማቅረብና እገረ መንገዱንም ለሀ/ስከቱ ማደራጃ የሚሆን ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚያስችል የ፪ ቀን መንፈሳዊ ጉባዔ (ነሐሴ ፴ እና ጳጉሜን ፩ ቀን ፳፻፯ ዓ/ም) የሀ/ስከቱ መንበረ ጵጵስና በሚገኝበት ሮሰልስሀይም-ጀርመን የተዘጋጀ ሲሆን ጉባዔው በቤ/ክናንና በምእመናን በተለይም በስደት ሀገር ተበታትነው በሚኖሩት መካከል ያለውን የእናትና ልጅነት ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር መንፈስ እንደሚፈጥር ይጠበቃል። በቀጣዩ ዓመትም በሌሎች ሀገሮች ተመሳሳይ መርሐ ግብሮች ይከናወናሉ።

በሀ/ስከቱ የሰ/ት/ቤት ማደራጃ መምሪያ የማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ቅርንጫፍ በኩል የተከናወኑ፡

1/ ትምህርተ ወንጌልን ለማስፋፋት ከአጥቢያ አ/ክናት ጋር በመተባበር ጉባ ዔያት ተዘጋጅተዋል፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢና በፓልቶክ ትምህርት እንዲሰጥ የተደረገ ሲሆን በሀ/ስከቱ ውስጥ የሚገኙና ከሀገር ቤት የተጋበዙ መምህራን ትምህርትና ምክር በመስጠት ተሳትፈዋል፤ የትምህርትና የጸሎት መጻሕፍት ለምእመ ናን እንዲቀርቡም ጥረት ተደርጓል፤

2/ በሀገር ቤት ላሉ ገዳማትና የአብነት ት/ቤቶች ድጋፍ ለማሰባሰብ የገዳማትንና የአብነት ት/ቤቶችን የሚያስተዋውቁ ቅስቀ ሳዎች ተደርገዋል፤ የሐዊረ ፍኖት ዓመታዊ ጉባዔን ጨምሮ በበርካታ አጥቢያዎች ጉባዔያትና ዐውደ ርእዮች ተዘጋጅተዋል፤ የገዳማት ምርቶችም ለሽያጭ ቀርበዋል፤

3/ በ፹፬ የተመረጡ አርእስት ፪ የሕፃናት ማስተማርያ ጽሑፎች ተዘጋጅተዋል፤ የሕፃናት ማስተማርያ መዋቅር ጥናትም አዘጋጅቶ ለሀ/ስከቱ ለማስረከብ በዝግጅት ላይ ይገኛል፤

4/ በኢትዮጵያ ጠረፋማ አካባቢዎች ለሚደረገው የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ማጠናከሪያ የሚሆን ገንዘብ ተሰብስቦ እንዲላክ ተደርጓል፤ በተመሳሳይ መልኩ ለሞጣ ደ/ገ ቅ/ ጊዮርጊስ የላይ ቤት መጻሕፍት ትርጓሜ ቤት ሙሉ ወጪ በመሸፈን የመማሪያና የማደሪያ ክፍሎች ያሉት ባለ ፩ ፎቅ ሕንፃ እንዲገነባ ተደርጓል፤ ለነቀምቴ ምስካበ ቅዱሳን ዑራኤል ወሳሙኤል ዘዋልድባ ገዳም የአብነት ት/ቤትና ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ሁለገብ ሕንፃ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል፤ ለተወሰኑ የአብነት መምህራንና ተማሪዎችም ወርኃዊ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል እየተደረገም ይገኛል፤

5/ በአውሮፓ ከተሞች የሚኖሩ ምእመናንን ተደራሽ የሚያደርግ የራዲዮ አገልግሎት ትግበራ ጥናት በመደረግ ላይ ነው፤

6/ በአውሮፓ ከሚገኙት 2ቱም ሀ/ስከቶች ጎን በመቆም በሚያስፈልገውና በሚታዘዘው ሁሉ እያገለገለና ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የሀ/ስከቱ አካል እንደመሆኑ መጠን ይህንኑ አገልግሎት አጠናክሮ ይቀጥላል።

በሀገረ ስብከቱ የ፳፻፯ ዓ/ም የሥራ ዘመን ያጋጣሙ ዐበይት ችግሮች

ሀገረ ስብከቱ ምንም እንኳ የቤተ ክርስቲያን አምላክ የክርስቶስ ኢየሱስ ፍጹም ረድኤት ሳይለየው ከላይ የተዘረዘሩትንና ሌሎችንም ተግባራት ለማከናወን ቢችልም እንቅስ ቃሴውን የሚገድቡና የሚቃረኑ ካመቸም የሚያኮላሹ በርካታ ችግሮች ሳያጋጥሙት እንዳልቀሩ በዚህ አጋጣሚ ለዚህ ጉባዔ ሳይንገልጽ አናልፍም። ችግሮችን ሁሉ አንድ በአንድ መግለጽ አላስፈላጊ ባይሆንም መፍትሔ ሊፈለግላቸው እርምት ሊደረ ግባቸው ይገባል ተብሎ የሚታመንባቸውን እንጠቁማለን።

1/ በ፳፻፮ ዓ/ም በውይይት ተፈታ ተብሎ ይታሰብ የነበረው የሀ/ስከቱ በድጋሚ አወቃቀር ሂደት ላይ ጥያቄና ቅሬታ በሰኔ ወር ፳፻፯ ዓ/ም ከለን ላይ በተደረገ የወረዳ ቤ/ክህነት ስብሰባ ላይ በድጋሚ ውይይት ተደርጎበት ላያዳግም መፈታቱ ቢገለጽም ክረቱ በቁጥር ጥቂት የማይባሉ ምእመናን ለሀ/ስከቱ ቀና አመለካከት እንዳይኖራቸውና ከመተባበር እንዲታቀቡ አድርጓቸው ቆይቷል። በዚህም ሳቢያ የተወሰኑ አድባራት ከሀ/ስከቱ ጋር አብሮ ለመሥራት ሙሉ ፈቃደኝነት ሳያሳዩ ከመቆየታቸው በተጨማሪ ምንም ዓይነት የገንዘብ ፈሰስ አላደረጉም። ይህም የሀ/ስከቱን እንቅስቃሴ በእነዚህ አካባቢዎች ገድቦት የቆየ ሲሆን አሁን እየታየ ያለውን የመለስለስ አዝማሚያ አጎልብቶ ሙሉ በሙሉ ለማስተካከል ገና ብዙ ሥራ የሚያስፈልገው ጉዳይ ሆኖ ይታያል። በአጥቢያ በኩል ለሕዝብ የሚተላለፉ መልእክቶች ለምእመናን በትክክል የማይተላለፉባቸውና ቅሬታ በሚያስከትል መልኩ ተዛብቶ የሚነገርባቸው ቦታዎችም አጋጥመዋል፤ ይህም እልባት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።

2/ በቃለ ዓዋዲ ድንጋጌ መሠረት ሀ/ስከት የሚተዳደረው አድባራት ከገቢያቸው ላይ በሚያደርጉት የገንዘብ ፈሰስ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም መሠረት ለጊዜው በቃለ ዓውዲ ሕግ መሠረት ፈሰስ ለመሰብሰብ አድባራቱ ያሉበት ሁኔታ ፈጽሞ የማይፈቅድ በመሆኑ አድባራቱ እንደ ገቢያቸው መጠን በ፫ ተደልድለው በየወሩ ከ፶ እስከ ፻፶ ኦይሮ ድረስ ፈሰስ እንዲያደርጉ በጋራ ስምምነት ተወስኗል። በርካታ አድባራት በዚሁ መሠረት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ እያስተላለፉ ቢሆኑም በተቃራኒው ጭራሽ መክፈል ያልጀመሩና አሟልተው ያልከፈሉ አድባራት ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም። ይህም ሀ/ስከቱ ከኢኮኖሚ ችግር መላቀቅ እንዳይችል ከማድረጉም በላይ ወሳኝ የሆኑ ተግባራትን እንኳ ለማከናወን የማይቻልበት ሁኔታ ተከሥቷል። በመሆኑም ክፍያ ያለጀመሩና ያላሟሉ አድባራት የሚጠበቅ ባቸውን ፈሰስ እንዲያስገቡ የሚደረግበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል።

3/ ሀ/ስከት በብዙ አካባቢዎች ተሸፍኖ የቆየና አድባራት በበላይ መ/ቤት ሊወሰኑና ፈቃድ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ሁሉ በየራሳቸው ሲፈጽሙ በመቆየታቸው ይህንን ልማድ ቀስ በቀስ ለማስተካከል ጥረት ተደርጓል እየተደረገም ይገኛል። ይሁን እንጂ አሁንም የተወሰኑ አድባራት በተዋረድ ሀ/ስከት ሊቀርቡ የሚገቡ ጉዳዮችን ራሳቸው ሲጨርሱ ወይም ሀ/ስከቱን አልፈው በቀጥታ ወደ መ/ፓጠ/ቤ/ክህ ሲወስዱ ይታያል። ለምሳሌም የሰ/ጉ ምርጫ ከተደረገባቸው ፭ አድባራት መካከል ፫ቱ ብቻ ምርጫውን አስፈቅደው ያካሄዱና የጸደቀላቸው ሲሆን የቀሪዎቹ ግን በተለመደው አሠራር ሄዷል። በመሆኑም ማዕከልን የጠበቀና ሕግን የተከተለ አሠራር ሁሉንም ወገን ከስህተት የሚጠብቅና ሕጋዊ የሚያደርግ በመሆኑ እርማት ሊደረግበት ይገባል።

4/ የማጥመቅ ፈቃድ አለኝ በሚል ትክክለኛ ያልሆነ ደብዳቤ እየተንቀሳቀሱ ያሉት መ/መ ግርማ በተደጋጋሚ ወደ ሀ/ስከቱ የአስተዳደር ክልል መመላለሳቸው ሌላው የዓመቱ ችግር ሆኖ አልፏል። ግለሰቡ ቤ/ክ ፈቃድ ስላልሰጠቻቸው በየትኛውም ደብር እንዳያገለግሉ መታገዳቸውን የሀ/ስከቱ ጽ/ቤት ከማስረጃ ጋር ለአድባራት ፪ ጊዜ ያህል ያስታወቀ ቢሆንም በደብር ደረጃ ፩ ደብር እንዲሁም በግለሰቦች ማኅበር ደረጃ ሙኒክ ላይ እገዳውንና መመሪያውን በመጣስ ግለሰቡ ተጋብዘዋል። በተለይም በሙኒክ በተነሣው ግርግር ጥቅመኞች አስከልክለዋል ብለው በገመቷቸው የደብሩ አስተዳዳሪ ላይ የተቋውሞ ሰልፍ እንዲወጣ አድርገዋል ክብረ ነክ ስድብና የስም ማጥፋት ወንጀልም ፈጽመዋል። ሀ/ስከቱ ጉዳዩን ለመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክህ በማሳወቅ ተገቢው ርምጃ እንዲወሰድ በአጽንኦት የጠየቀ ሲሆን ጉዳዩ ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ ውሳኔ እንዲያገኝ በአጀንዳነት ተይዟል። መመሪያ በመጣስ ግለሰቡን ለጋበዘው ደብርና ለደብሩ አስተዳዳሪም በጽሑፍ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል። ይሁን እንጂ ይህ ሙከራ ተመሳሳይ ፍላጎትና ዓላማ ላላቸው የጥቅም ሰዎች በር ከፋች መሆኑ አልቀረም፤ ስለዚህም ነው ፈዋሽ ባሕታዊ ነኝ የሚሉ ሌላ ግለሰብ እንዲሁ ከሆላንድ ወደ ጀርመን መጥተው ከሀ/ስከቱ ውጪ በሆነ ደብር ተጠግተው ምእመናን በሚጎዳና የሃይማኖትን ክብር በሚጻረር ሁኔታ አሳዛኝ ተግባር ሲፈጽሙ ሰንብተው የሄዱት። ሀ/ስከቱ አጥቢያውን ማዘዝ ባይችልም በሀ/ስከቱ የፌስቡክ ፔጅ ተግባሩን በመቃወም ምእመናን ተባባሪ ከመሆን እንዲቆጠቡ ግልጽ ማሳሰቢያ አስተላልፏል፤ ይህም ግልሰቡ ጀርመን ውስጥ ያደረጉት እንቅስቃሴ ሆላንድ እንዳደረጉት ውጤታማ ሳይሆንላቸው እንዲቀር አድርጓል። ሆኖም ይህ አደገኛ ሁኔታ ዳግም እንዳይከሠት ለማድረግ በተለይ የአድባራት አስተዳዳሪዎችና ካህናት ከልብ ከሀ/ስከቱ ጎን በመቆም ምእመናንን በግልጽ ማስተማርና መድረክን መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

የ፳፻፰ ዓ/ም የሥራና የአገልግሎት ዘመን ዕቅድ

በ፳፻፰ ዓ/ም የሥራና አገልግሎት ዘመን ሀ/ስከቱ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ አቅሙን አጠናክሮ ለመንቀሳቀስና የተሻለ የሥራ ፍሬ ለማሳየት የተዘጋጀ ሲሆን ረድኤተ አግዚአ ብሔርን አጋዥ በማድረግ በዋናኝነት የሚከተሉትን ተግባራት ለማከናወን አቅዷል፡
1/ የሀ/ስከቱ ረቂቅ የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ በፍ/ቤት ጸድቆ ተግባር ላይ እንዲውል ማድረግ፤
2/ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ስም የአገልግሎትና የትምህርት ማዕከል የሚሆን ገዳም ለማቋቋም የተጀመረውን እንቅስቃሴ ዳር በማድረስ አንድ ገዳም እንዲቋቋም ማድረግ፤
3/ አማርኛ ወይም ግእዝ የማይሰሙ ዜጎች የቅዳሴ ጸሎት በመጽሐፍ ወይም በፕሮ ጄክት እንዲከታተሉ ለማስቻል ይረዳ ዘንድ ሙያዊና ኢኮኖሚያዊ ርዳታ በማፈላለግ የቅዳሴ መጽሐፍ በጀርመንኛ፣ በፈረንሳይኛ እና በጣልያንኛ ቋንቋ በቅደም ተከተል እንዲተረጎም ማድረግ፤
4/ በአውሮፓ ለተወለዱ ሕፃናት ማስተማሪያ የሚሆን የትምህርት መረጃ በአማርኛና እንግሊዝኛን ጨመሮ ከላይ በተጠቀሱት ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ እንዲሠ ራጭ ማድረግ፤
5/ በሀ/ስከቱ የሰ/ት/ቤት ማደራጃ መመሪያ ሥር ከሁሉም አድባራት የተውጣጡ አባላት ያሉት የመዘምራን/ት ክፍል አቋቁሞ ማሠልጠንና በክፍሉ አስተባባሪነት አባላቱ በየመጡበት ደብር የሚገኙትን የሰ/ት/ቤት መዘምራን በቤ/ክ የተፈቀዱና ኦርቶዶክሳዊ ለዛቸውን የጠበቁ መዝሙሮችን ብቻ እያ ጠኑ እንዲዘምሩ እንዲያስተባብሩ፣ እንዲያስ ጠኑና እንዲቆጣጠሩ ማድረግ፤
6/ በዓመቱ የትምህርት መዝጊያ ወቅት ላይ ለ15 ቀናት የሚቆይ የአሠልጣኞች ሥልጠና ከየደብሩ ለሚውጣጡ ዲያቆናትና የሰ/ት/ ቤት መርሐ ግብር መሪዎች መስጠት፤
7/ ልዩ ልዩ መርሐ ግብሮችን ባካተተና አውሮፓውያንን ተሳታፊ ባደረገ መልኩ የቅዱስ ያሬድን መታሰቢያ በዓል ከጀርመን ጀምሮ በየክልሉ በተራ በየዓመቱ በጋራ እንዲከበር ማድረግ፤
8/ በበርሊን ደብረ ገነት አማኑኤል ቤ/ክ የደብሩን ሰ/ጉ ጽ/ቤት በቅርብ በማገዝ አንድ ቤተ መጻሕፍት ተከፍቶ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ፤
9/ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ቁጥር በተለይ ወደ ጀርመን የገቡት ስደተኞች የአልባሳትና የቁሳቁስ ርዳታ ሊደረግላቸው እንደሚገባ እየተነገረ በመሆኑና ቤ/ክም እንዲህ ላለው ሃይማኖታዊና ሰብአዊ ተግባር ግንባር ቀደም አርአያ መሆን ስለሚገባት በየአጥ ቢያው አልባሳትና ቁሳቁስ ተሰብስቦ ስደተኞቹን የሚያስተናግዱ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ የርዳታ ድርጅቶች በሚያውቁት መልኩ ርዳታ እንዲለገስ ማስተባበር፤
10/ የቤ/ክን ይተከልልን ጥያቄ እያቀረቡ ያሉ የ፬ ጽዋማኅበራትን ጥያቄ ከላይ በሪፓርቱ በተገለጸው መሠረት አጥን ቶና አስጠንቶ ተገቢውን ምላሽ መሰጠት።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

ነሐሴ ፳፱ ቀን ፳፻፯ ዓ/ም

ሮሰልስሀይም- ጀርመን

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *