የብፁዕ አቡነ ሙሴ ቃለ ምእዳን ፳፻፰ ዓ/ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በቅርብም በሩቅም ያላችሁ ሕዝበ ክርስቲያን የመንፈስ ልጆቼ ቸርነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ በሰላም አደረሳችሁ፤ አዲሱን ዘመን የሰላም የበረከትና የጤና ዘመን ያድርግልን።

እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ዘመን ከአራት ይከፈላል፥ ከመስከረም ፳፮ እስከ ታኅሳስ ፳፭ የነፋስ ወራት፣ ከታኅሳስ ፳፮ እስከ መጋቢት ፳፭ የእሳት ወራት፣ ከመጋቢት ፳፮ እስከ ሰኔ ፳፭ የተዘራ የሚበቅልበት የመሬት ወራት፤ በስያሜም ጸደይ፣ መጸው በጋ እና ክረምት ይባላሉ። እኒህም የሰው ዕድገት ምሳሌዎች ናቸው በአራት ይከፈላልና ከ፯ እስከ ፳ ያለው የእሳት ዘመን ነው ከ፳ እስከ ፵ ያለው የእሳት ዘመን ነው ከ፵ እስከ ፷ የውኃ ዘመን ነው ከ፷ እስከ ፹ የመሬት ዘመን ነው።

ልበ አምላክ ዳዊት “ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ ፥ የምሕረትህን ዓመት አኪልል ትባርካለህ“ መዝ ፷፬፥ ፲፩ እንዳለ መዐልትና ሌሊትን፤ ክረምትና በጋን የሚያፈራርቀው ዘመንን አሳልፎ አዲስ ዘመን የሚያመጣው በጊዜ ሠረገላም የሰውን ዘር ሁሉ በደኅነንት ጠብቆ በአካል በአእምሮ አልቆ ከዘመን ወደ ዘመን የሚያሸጋግረው የሁሉ አስገኚና የሁሉ መጋቢ የሆነ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ነው። የሰዓታትን፣ የዕለታትን፣ የሳምንታትን፣ የወራትንና የዓመታትን መለዋወጥ የጊዜ ለውጥንም ተከትለው በዓለም ላይ ሰውን ሌላውንም ሥጋዊና ደማዊ ፍጥረት ሁሉ ለመ መገብ የሚፈራረቁ ክስተቶችን ባስተዋልን ጊዜ የሰማይና የምድር ፈጣሪና ጌታ የአምላካችን የእግዚአብሔርን ሀልዎትና ቸርነት እንገነዘባለን ቸርነቱንና ከኃሊነቱንም በፍጹም ክብር እናመ ሰግናለን። ምክንያቱም ይህ ሁሉ በሥርዓት ለመሆኑ ለመከናወኑ የሰው ልጅ አንዳችም ድርሻ ወይም ተሳትፎ የለውም ጊዜያትን የሚያፈራርቀው የሰውንም ልጅ ራሱን ከጥፋት ጠብቆ የሚያኖረው የልዑል አምላክ ፍጹም ቸርነቱ ነውና።

እንደእኛ እንደ ሰው ልጆች አሳብና ተግባር ቢሆን ኖሮ የልባችን ተንኮል የሥራችን ክፋት በኖኅ ዘመን እንደነበሩ ሰዎች ጥግ በደረሰበት፤ እንደ ሰዶምና ጎሞራ ከተሞች ዓለም መላዋ የክፉ ኃጢአትና ወንጀል መዲና በሆነችበት፤ ንጹሐን በግፍ ሲሰደዱ ሲታረዱ ዓመጸኞች በፌሽታና በፈንጠዝያ የድኆችንም ዕንባ በማፍሰስ በሚሳከሩበት በእኛ ዘመን በእኛ ትውልድ መዐልትና ሌሊት ክረምትና በጋ አንፈራረቅም ባሉ፤ ዝናማት ባልዘነሙ ውኆች ባልፈ ሰሱ፤ ፀሐይ ዓለምን ባላሞቀች፤ ጨረቃና ከዋክብትም የሰማይን ሰሌዳ በብርሃናቸው ለማድመቅ ባልወጡ፤ ዘመን ባልሄደ ዘመን ባልተተካ ነበር።

አዎን እንደ አዳም ልጆች አሳብና ሥራ ቢሆን እግዚአብሔርን መፍራት ስንኳን ካላመኑት ካመኑትና በስሙ ከተጠሩትም ወገኖች ሁሉ በጠፋበት መተማመን መተዛዘን ተኖ ኃይለኞችና ብልጣብጦች ብቻ ዓለምን እንዳ ሻቸው በሚገዙበት የእግዚአብሔር ድኆች ወገኖች ድንበር በሌለው የመከራ አሮንቃ ወስጥ ዘቅጠው በሚቃትቱበት በዚህ ዓመፀኛ ትውልድ በሙሴ ዘመን ለእስራኤላ ውያን በቀንና በሌሊት የሚመራቸው ብርሃን ሲታዘዝላቸው በግብ ጻውያን ጨለማ እንደታዘዘባቸው ሁሉ ፀሐይ ለጥቂት ደጋጎች ብቻ ወጥታ ሌላውን ጨለማ በዋጠው፤ ለጥቂት ንጹሐን ብቻ ሙቀት ልምላሜ ሲታዘዝላቸው ሌላውን ዓለም ቁርና አስሐትያ ማዕበልና ሞገድ በዋጠው ባቀለጠው ነበር። ነገር ግን ይህ አልሆነም አይሆንምም፤ አምላካችን እንደ ሰው ያይደለ እንደራሱ ባሕርይ በቸርነት በይቅርታ ጸንቶ የሚኖር ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅ የታመነ አምላክ ነውና። በኦሪት “ወይቤ እግዚአብሔር ኀለይኩ ከመ ኢይድግም ረጊሞታ ለምድር በእንተ ምግባሩ ለእጓለእመሕያው ፥ እግዚአብሔርም አለ ፥ ዳግመኛ ምድርን በሰው ልጆች ሥራ ምክንያት አላጠፋትም አልሁ“ ዘፍ ፰፥፳፩ ተብሎ እንደተጻፈ ምድርን እንዳያጠፋት ይልቁንም ጥንቱን ከታዘዘላት በረከት አንዳች እንዳይጎድልባት ለባለሟሉ ለኖኅ የገባለት ቃል ኪዳን ነበር። እንግዲህ መዐልትና ሌሊትን ፀሐይና ጨረቃን ክረምትና በጋን የሚያፈራርቀው ልዑል ጌታ ይህን ቃል ኪዳኑን ለመጠበቅ ያለው ቅዱስ ፈቃድ ነው። ነፋሱን የምሕረት ነፋስ ዝናሙም የምሕረት ዝናም የሚያደርገው ለምድር ልምላሜዋን የሚሰጠው በርግጥ የቸርነት የይቅርታ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለዚህ ነው የቀኑ ሰዓት ሲያልቅ የሌሊቱ ሰዓት ሲመጣ ክረምቱ ሲፈጸም በጋው ሲመጣ ጨረቃ ዘወር ስትል ፀሐይ ስትወጣ ፍቅር የተሞላበት ያማረና የተወደደ ቅዳሴያችንን ውዳሴያችንን ይዘን በፈጣሪያችን ፊት ለምስጋናና ለአምልኮት የምንቆመው የምናደገድገው።

በዓለም ላይ አንዲት ቀን ያለፈጣሪው ቸርነት በገዛ ፈቃዱና ችሎታው ለመዋል ወይም አንዲት ሌሊት ለማድር አቅም የሌለው ፤ ነፋስንና ፀሐይን በፈለገበት ጊዜ፣ ቦታና መጠን ለማግኘት አንዳችም ዋስትና የሌለው የሰው ልጅ የትም የማያደርስ ትዕቢቱንና መመካቱን ትቶ ከመከራ ሁሉ ጠብቆ ከጥፋት ታድጎ ሳይገባው በዕድሜ ላይ ዕድሜ በበረከት ላይ በረከት እየጨመረ የሚያኖረውን የፈጣሪውን ውለታና ቸርነት ቢያስተውለውና ቢገዛለት አንድ ዘመን ብቻ አይደለም የብዙ ብዙ ዘመናት ጨምሮ ጨማምሮ በምድር ላይ ባኖረው፤ የምድሩን ፍሬ በባረከለት፣ በረቱን በእንስሳት ጎተራውን በእህል በሞላለት፤ ድንጋጤንና መታወክን አስወግዶ ሰላምና ጸጥታን ባሰፈነለት ነበር። በምድር ላይ ስጋትና ሁከት የሌለብት ሰላማዊ ኑሮ ለመኖር ድሮም የሰው ልጅ ያለው አስተማማኝ አማራጭ የእግዚአብሔርን ቸርነት ተጠግቶ መኖር ብቻ ነው። የእግዚአብሔርን ቸርነት ተጠግቶ ከመኖር ይልቅ የራሱ ጥገኛ ሆኖ መኖርን የመረጠ ሕዝብ ጌታ በወንጌል “እስመ ውእቱ ያሠርቅ ወያዐርብ ፀሐየ ላዕለ ጻድቃን ወኃጥአን ፥ እርሱ ፀሐይን ለጻቃንም ለኃጥአንም ያፈራርቃልና“ ማቴ ፭፥፵፭ እንዳለ የፀሐይን ብርሃን የሰማይን ጠል ለደጋጎቹ ሲሰጥ ባይነፍገውም መቼም ቢሆን ከስጋት ነጻ የሆነ ዕረፍትና ርካታ ያለበት ውሎ ሊወል ኑሮ ሊኖር ግን አይችልም፤ ለሰው ልጅ ብቻ ያይደለ ነፍስ ላላቸው ፍጥረታት ሁሉ አስፈላጊ የሆኑ የመኖር ዋስትና ያላቸው ነገሮች ሁሉ በእግዚአብሔር እጅ ናቸውና፤ ፀሐዩ፣ ዝናሙ፤ ነፋሱ፤ በጥቅሉ ዓለምና መላዋ የእግዚአብሔር ናትና። መዝ ፳፫፥፩ ወጥተው ወርደው የሰበሰቡት አርሰው ያመረቱት ነግደው ያተረፉት እንኳ ቢሆን የእግዚአብሔር ስጦታ እንጂ የሰው ልጅ የድካሙ ውጤት ብቻ አይደለም ፤ እርሱ ባለቤቱ ካልፈቀደም ይሰበሰባል እንጂ አይበላም ሰሎሞን “ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት በድካሙም ለሰውነቱ መልካም ነገር ከሚያሳያት በቀር በጎ ነገር የለም፤ ይህ ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደተሰጠ አየሁ“ እንዳለ። መክ ፪፥፳፬ ጎተራውን በምድር በረከት መልቶ ነፍሴን እንግዲህ ብዪ ጠጪ እላታለሁ እያለ የተቀማጠለ ኑሮ ለመኖር ፕላን ባወጣበት ሌሊት “አንተ ሰነፍ ሰው በዚች ሌሊት ነፍስህን ከሥጋህ ለይተው ይወስዷታል እንግዲህ የሰበሰብኸው ሁሉ ለማን ይሆናል?“ የተባለውና የተባለውም የተፈጸመበት ፈጣሪውን በሥራው ሁሉ በኑሮውም ሁሉ የዘነጋና የራሱ ጥገኛ የሆነው ባለጸጋ ታሪክም ይህንኑ የሚያስረዳ ነው። ሉቃ ፲፪፥፳፬

የተወደዳችሁ ሕዝበ ክርስቲያን! ውጥን ፍጻሜ የሚያገኘው ሥራም ሁሉ በመልካም ሁኔታ ሊሠራ የሚችለው በእግዚአብሔር ፈቃድና አጋዥነት ነው፤ ሰው ብቻውን ቢሮጥ አይቀድምም፤ ብቻውን ቢደክም ውጤታማ አይሆንም፤ እግዚአብሔርን መያዝ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ለምእመናን ብቻ ሳይሆን ለሰው ሁሉ አስፈላጊ ነው። እርሱ ሲፈቀድ የተበላሸው ይታደሳል የጠመመው ይቃናል፤ ፈቃዱ ካልሆነ ቸርነቱ ከተለየ ግን ጳጉሜን ብሎ መስከረም ማለት የማይቻል ሊሆን ይችላል፤ ተኝቶ መነሣትም ላይሳካ ይችላል፤ ለዚህም በየጊዜው ነፋስና ማዕበል ሞገድና ጎርፍ እየጠራረገ የደንጊያ ክምር የሚያደርገውን የከተማና የመንደር ብዛት፤ ከሞቀ ጎጃቸው እያፈናቀለ ከሜዳ የሚያፈሳቸው ወገኖችን ሁኔታ መለስ ብሎ ከማየት የበለጠ ማስረጃ ሊኖረን አይችልም፤ የሰው ሥራ ሁሉ እየተለወጠ ነው እግዚአብሔር ያለው እርሱ እንዳይሆን ማገድ መከልከል የተቻለው ማንም ኃያል አልተገኘም ሊገኝም አይችልም። በመሆኑም የሚሻለን የሚገባንም የዕለታት የዓመታት መፈራረቅ ልማዳዊ ሂደት ሳይሆን የእግዚአብሔር አምላካዊ መግቦት መሆኑን አምነን “አንተ ፈጠርከ ፀሐየ ወወርኀ ፥ ፀሐይና ጨረቃን የፈጠርክ አንተ ነህ“ ወአንተ ገበርከ አድባረ ምድር ኵሎ ፥ ተራራውን ኮረብታውን ሁሉ የፈጠርህ አንተ ነህ፡ ክረምተ ወሐጋየ ዘአንተ ፈጠርከ ፥ ክረምትና በጋን የፈጠርህ አንተ ነህ። ለከ ውእቱ መዐልት ወዚአከ ይእቲ ሌሊት ፥ አሥራ ሁለት ሰዓተ ሌሊት አሥራ ሁለት ሰዓት መዐልትም የአንተ ሥራዎች ናቸው“ ብለን የቸርነቱን ብዛት ማድነቅ ማመስገን ለስሙም መገዛት የቸርነቱ ጥገኛ የፍቅሩ ምርኮኛ ሆኖ መኖር ነው። ዘፍ ፩፥፩፣ ፲፬ መዝ ፸፫፥፲፮

ዘመን አልፎ አዲስ ዘመን ሲተካም በዕድሜያችን ላይ ዕድሜ እንደተጨመረልን ብቻ ሳይሆን የሰው ዘር ሁሉ በጨለማ አገዛዝ ሥር ወድቆ መከራ ነፍስ የተቀበለበትን የፍዳ የመርገም ዘመን ያሳለፈባት ክብርና ብልጽግናን ዘለዓለማዊ ሕይወትንም ያጎነጸፈባት አምላካችን ፍጹም ቸርነቱንና ይቅርታውንም በደሙ ፈሳሽነት ያደለባት የተመረጠች አዲሲቱን የእግዚአብሔር ዓመትም እናስታውሳለን። “ፈነወኒ እስበክ ሎሙ ዓመተ እግዚአብሔር ኅሪተ ፥ የተመረጠችውን የእግዚአብሔር ዓመት እሰብክ ዘንድ ላከኝ “ ተብሎ የተነገረላትን ኢሳ ፷፩፥፩ ሉቃ ፬፥፲፮ የሰው ልጅ ከባርነት ወደ ነፃነት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገረባትን የተመረጠች ዓመት አዲስ ዘመን ዘመነ ሥጋዌን እንመሰክራለን፤ ወገኖቼ የመንፈስቅዱስ ልጆቼ ! ውሽንፍር ጎርፍ ከበዛበት የክረምት ጊዜ ሙቀት ልምላሜ ወደሚታይበት ወደ በጋ አምላክ ሲያሸጋግራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ መሥዋዕትነት ከመከራ ከሥቃይ ዘመን የመንፈስቅዱስ ልጅነት ወደሚሰጥበት ዓመት ምሕረት ዓመት ሣህል የሻጋገራችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች መሆናችሁን አስቡ፤ በሥራችሁ በኑሮአችሁ ሁሉ ይህን ቸር አምላክ ደስ ለማሰኘት ትጉ፤ ፈቃዱን ለመጣስ ከቶ አትድፈሩ፤ ደስታችሁ እርሱን ደስ በማሰኘት ክብራችሁም እርሱን በማክበር የሚገኝ ነውና ደስ የሚያሰኛችሁን ብቻ ያይደለ ፈጣሪያችሁን ደስ የሚያሰኘውን በጎ ሥራ ለመሥራት፤ እርሱን ደስ በሚያሰኘው ሥፋራ ለመዋል፣ ደስ የሚያሰኘውን የተቀደሰ ክርስቲያናዊ አኗኗር ለመኖር እንድትተጉ እመክራችኋለሁ። ቸር አምላክ ዘመኑን የምሕረት የይቅርታ የበረከት የሰላም ዘመን ያድርግልን ፤ ለዓለሙ ሁሉ ሰላምን ያድልልን፤ ሀገራችንና ሕዝባችንንም ከመከራ ሥጋ ይጠብቅልን።

እግዚአብሔር አምላክ ይባርከን ይቀድሰን። አሜን

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *