“ተፋቀሩ ዘልፈ እስመ ማእሠረ ተፍጻሜቱ ውእቱ — ዘወትር በፍቅር ኑሩ የመጨረሻው ማሠሪያ እሱ ነውና።” ቆላ ፫፥፲፬

የብፁዕ አቡነ ሙሴ

የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የመላው አውሮፓ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳን

መስከረም ፳፻፲ ዓ/ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

የተከበራችሁ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ምእመናንና ምእመናት እንዲሁም የሰ/ት/ቤት ወጣት መዘምራን መዘምራት፥ ቸርነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ የዕለታትና የዓመታት የጊዜያት ሁሉ ባለቤት በአንድነት በሦስትነት ሲመሰገን የሚኖር አምላካችን እንኳን ሁላችንንም በሰላምና በጤና ጠብቆ ከዘመነ ማቴዎስ ወደዘመነ ማርቆስ አሸጋገረን! አዲሱን ዘመን የምሕረትና የይቅርታ የሰላምና የበረከት ዘመን ያድርግልን።

ከላይ በመግቢያዬ የጠቀስሁት አምላካዊ ቃል ሐዋርያ ሰላም መምህረ አሕዛብ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ በወህኒ ቤት ታሥሮ ሳለ በቆላስይስ ለነበሩ በኤጳፍራስ ትምህርት ካለማመን ወደማመን ለመጡ በተማሩትም ትምህርት ጸንተው አምላካቸው እግዚአብሔርን በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ሲያገለግሉት ለመኖር ቁርጠኛ አሳብ ለነበራቸው ከቅዱሳንም ጋር ለትምህርተ ወንጌል መስፋፋት ለሃይማኖተ ክርስቶስ መበልጸግ ይተጉ ለነበሩ ምእመናነ ወንጌል ከሃይማኖት ከበጎ ሥራ ፈቀቅ የሚያደርግ እንቅፋት ሳይገጥማቸው በበረከት ላይ በረከት በጸጋ ላይ ጸጋ እየተጨመረላቸው ይኖሩ ዘንድ ለመምከርና ለማትጋት ጽፎ ከላከላቸው ቃለ ምዕዳን ውስጥ የተገኘ አምላካዊ ቃል ነው።
ሐዋርያው መልእክቱን የሚጀምረው የምእመናኑን እምነት፣ በጎነት፣ ደግነት፣ ትጋትና የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት መትጋታቸውን በተወደደ ቃል በማመስገን ነው። Read more

የብፁዕ አቡነ ሙሴ ቃለ ምእዳን ፳፻፱ ዓ/ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

የተወደዳችሁ አዕይንት እግዚአብሔር ካህናት እና አባግዐ ክርስቶስ ምእመናን፤ ቸርነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር እንኳን በሰላምና በጤና ጠብቆ ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ አሸጋገራችሁ፤ አዲሱ ዘመን የሰላምና የበረከት ዘመን ይሁንላችሁ።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንከሰ ጽንዑ በእግዚአብሔር ወበጽንዐ ኃይሉ ወልበሱ ወልታ እግዚአብሔር በዘትክሉ ተቃውሞቶ ለመናስግተ ሰይጣን“ ትርጉም “ከእንግዲህስ ወዲህ በእግዚአብሔር ጽኑ፤ በኃይሉም ጽናት፤የሰይጣንንም ማሳት ታቸንፉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ጋሻ ልበሱ“ ሲል የኤፌሶንን ምእመናን ሰይጣን በተንኮል ከሚያመጣባቸው ጦር የሚድኑበት ብሎም ድል የሚነሡበትን የእግዚአብሔርን ጋሻ ገንዘብ እንዲያደርጉ መክሯቸዋል። ኤፌ ፮፥፲ ሐዋርያው ይህንን ምክር የመከራቸው ምእመናን በሥጋ ዓለም እንደሚደረገው ላለ ሥጋዊ ጦርነት ለማዘጋጀት አይደለም። ምእመናን በዓለም ሲኖሩ ክርስቶስን መስለን በሃይማኖት በምግባር ጸንተን እንኖራለን ስላሉ በዚህም ዓላማቸው ለሰይጣንና ለመልእክተኞቹ አጋንንት መገዛትን ስለካዱ የሚገጥማቸው ብዙ የሰይጣን መፈታተን መተነኳኮልና መከራ ያገኛቸው ዘንድ አይቀርምና ለመንፈሳዊ ሰልፍ በእምነት እንዲዘጋጁ ለማስጠንቀቅ ነው። ሰልፉም ሰውን ከማሳት በቃኝ ከማይል ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር እንጂ ከሥጋዊ ደማዊ ፍጥረት ጋር አለመሆኑ ሲገልጽ “እስመ ቀተልክሙ ኢኮነ ምስለ ዘሥጋ ወደም“ ትርጉም “ሰልፋችሁ ከሥጋዊ ከደማዊ አርበኞች ጋር አይደለምና“፤ “ዘእንበለ ምስለ መኳንንተ ጽልመት ወአጋንንት እኩያን እለ መትህተ ሰማይ“ ትርጉም “ዓለመ ጽልመትን ከሚገዙ ከአጋንንት ጋር ነው እንጂ“ ብሎ አስታውቋል። ሰው ከሰው ጋር የሚ ያደርገው ጦርነት በሥጋዊ ሰልፍ የሚሰለፉበት ቀላል ጦርነት ነው፤ ከአጋንንት ጋር የሚደረገው ጦርነት ግን በሥጋዊ ኃይል አቸናፊ የሚሆኑበት ጦርነት አይደለም። በዚህ ውጊያ ለማሸነፍ የሃይማኖት ኃይል ያስፈልጋል። ሐዋርያው “ወልበሱ ወልታ እግዚአብሔር“ ማለቱ ስለዚህ ነው። የጨለማውን ገዢ ሰይጣንን መልእከተኛው ዓለምንም ድል የሚነሣው በእምነት የጸና ብቻ ነውና “ወመኑ ውእቱ ዘይመውዖ ለዓለም ዘእንበለ ዘየአምን ከመ ኢየሱስ ውእቱ ወልደ እግዚአብሔር“ ትርጉም “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን ማቸነፍ የሚቻለው ማን ነው“ እንዲል። ፩ ዮሐ ፭፥፭ Read more

የ፳፻፱ ዓ.ም በዓለ ልደትን በማስመልከት ቅዱስ ፓትርያርኩ የሰጡት ቃለ ምዕዳን

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ዘተናገረ በእንተ በዓለ ልደቱ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት!!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

  • በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
  • ከሀገር ውጪ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
  • የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
  • በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
  • እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

እኛን ለማዳን በለበሰው ሥጋ በቤተ ልሔም ተወልዶ በመካላችን የተገኘው፣ በመለኮታዊ ባህርዩ የማይወሰነው አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት በዓለ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ!!

Read more

የብፁዕ አቡነ ሙሴ ቃለ ምእዳን ፳፻፰ ዓ/ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በቅርብም በሩቅም ያላችሁ ሕዝበ ክርስቲያን የመንፈስ ልጆቼ ቸርነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ በሰላም አደረሳችሁ፤ አዲሱን ዘመን የሰላም የበረከትና የጤና ዘመን ያድርግልን።

እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ዘመን ከአራት ይከፈላል፥ ከመስከረም ፳፮ እስከ ታኅሳስ ፳፭ የነፋስ ወራት፣ ከታኅሳስ ፳፮ እስከ መጋቢት ፳፭ የእሳት ወራት፣ ከመጋቢት ፳፮ እስከ ሰኔ ፳፭ የተዘራ የሚበቅልበት የመሬት ወራት፤ በስያሜም ጸደይ፣ መጸው በጋ እና ክረምት ይባላሉ። እኒህም የሰው ዕድገት ምሳሌዎች ናቸው በአራት ይከፈላልና ከ፯ እስከ ፳ ያለው የእሳት ዘመን ነው ከ፳ እስከ ፵ ያለው የእሳት ዘመን ነው ከ፵ እስከ ፷ የውኃ ዘመን ነው ከ፷ እስከ ፹ የመሬት ዘመን ነው።

ልበ አምላክ ዳዊት “ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ ፥ የምሕረትህን ዓመት አኪልል ትባርካለህ“ መዝ ፷፬፥ ፲፩ እንዳለ መዐልትና ሌሊትን፤ ክረምትና በጋን የሚያፈራርቀው ዘመንን አሳልፎ አዲስ ዘመን የሚያመጣው በጊዜ ሠረገላም የሰውን ዘር ሁሉ በደኅነንት ጠብቆ በአካል በአእምሮ አልቆ ከዘመን ወደ ዘመን የሚያሸጋግረው የሁሉ አስገኚና የሁሉ መጋቢ የሆነ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ነው። የሰዓታትን፣ የዕለታትን፣ የሳምንታትን፣ የወራትንና የዓመታትን መለዋወጥ የጊዜ ለውጥንም ተከትለው በዓለም ላይ ሰውን ሌላውንም ሥጋዊና ደማዊ ፍጥረት ሁሉ ለመ መገብ የሚፈራረቁ ክስተቶችን ባስተዋልን ጊዜ የሰማይና የምድር ፈጣሪና ጌታ የአምላካችን የእግዚአብሔርን ሀልዎትና ቸርነት እንገነዘባለን ቸርነቱንና ከኃሊነቱንም በፍጹም ክብር እናመ ሰግናለን። ምክንያቱም ይህ ሁሉ በሥርዓት ለመሆኑ ለመከናወኑ የሰው ልጅ አንዳችም ድርሻ ወይም ተሳትፎ የለውም ጊዜያትን የሚያፈራርቀው የሰውንም ልጅ ራሱን ከጥፋት ጠብቆ የሚያኖረው የልዑል አምላክ ፍጹም ቸርነቱ ነውና። Read more

አስተርእዮተ እግዚአብሔር በደብረ ታቦር

‹‹አስተርእዮ›› ሥርወ ቃሉ ‹‹አስተርአየ (አርአየ) = አሳየ፣ ገለጠ፣ ታየ፣ ተገለጠ›› የሚለው የግእዝ ግስ ሲኾን ትርጕሙም ‹‹መታየት፣ መገለጥ፣ ማሳየት፣ መግለጥ›› ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/፡፡ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር በደብረ ታቦር›› የሚለው ሐረግም ‹‹የእግዚአብሔር በታቦር ተራራ መገለጥ›› ወይም መታየት የሚል ትርጕም ያለው ሲኾን

Read more