እስመ ናሁ ተወልደ ለክሙ ዮም መድኅን ዘውእቱ ክርስቶስ እግዚእ ቡሩክ በሀገረ ዳዊት

“እስመ ናሁ ተወልደ ለክሙ ዮም መድኅን ዘውእቱ ክርስቶስ እግዚእ ቡሩክ በሀገረ ዳዊት ፥ እነሆ ዛሬ በዳዊት ሀገር መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ አምላክ ክርስቶስ ነው።” ሉቃ ፪ ፥ ፲፩

ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ምእመናንና ምእመናት በሙሉ፤ ዓለሙን ሁሉ ፈጥሮ የሚገዛ ለቸርነቱ ወሰን የሌለው አምላካችን እንኳን በሰላምና በጤና ጠብቆ ለበዓለ ልደቱ አደረሳችሁ ፥ አደረሰን።

በዓሉ የሰላምና የበረከት በዓል እንዲሆንላችሁ ከልብ እንመኛለን።

የሰላም አምላክ የይቅርታ ባለቤት ሀገራችንን፣ ሕዝባችንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ከክፉ ሁሉ ይጠብቅልን።

የም/ም/ደ አውሮፓ ሀገረ ስብከት
ጽ/ቤት

 

 

የምሥራቅ፣ ምዕራብና ደቡብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የ፳፻፱ ዓ/ም የሥራ ክንውን ዘገባ

እንደሚታወቀው ፳፻፱ ዓ/ም የሥራ ዘመን በሀገረ ስብከታችን ታሪክ በልዩ ሁኔታ ሲዘከር የሚኖር የሥራ ዘመን ነው። ልዩ የሚያደርገውም ቀደም ሲል በሀገረ ስብከቱ ውስጥ በልዩ ልዩ ኃላፊነት በማገልገል ላይ ከሚገኙት አባቶች መካከል እንደአገልግሎት ዘመናቸውና እንደ አገልግሎት ፍሬያቸው ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ትምህርታቸውንና አገልግሎታቸውን በዝርዝር የሚያስረዳ ሰነድ አዘጋጅቶ ለኤጲስ ቆጶስነት ምርጫ በእጩነት ካቀረባቸው ፮ አባቶች መካከል ፫ቱ የቅዱስ ሲኖዶስን ይሁንታ አግኝተው መመረጣቸውና ለመዐርገ ጵጵስና መብቃታቸው ሲሆን ሀገረ ስብከታችን ለእነዚሁ ለሌሎቹም በአንዲት ጉባዔ ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ከፍ ያለ ኃላፊነት ለጣለችባቸው ብፁዓን ጳጳሳት ሁሉ ዘመነ ጵጵስናቸው መልካም ፍሬ የሚያፈሩበት ይሆንላቸው ዘንድ ከልብ ይመኛል። Read more

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የምሥራቅ፣ ምዕራብ እና ደቡብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የ፳፻፰ ዓ/ም የሥራና አገልግሎት ክንውን ዘገባ

የደ/ም/ም አውሮፓ ሀገረ ስብከት በ2008 ዓ/ም የሥራ ዘመን በዓመቱ መጀመሪያ ላይ በምልዐተ ጉባዔ በጸደቀው የሥራ ዕቅድ መሠረት ለሀገረ ስብከቱና በሥሩ ለሚገኙ አድባራት ሥራና አገልግሎት መጠናከር አልፎ ተርፎም ለመላይቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መስፋፋት አስተዋጽኦ ያላቸው ተግባራትን ለማከናወን በ2007 የሥራ ዘመን ካደረገው ባልተናነሰ መልኩ ያላሳለሰ ጥረት አድርጓል።

ምንም እንኳ በአንዳንድ አድባራት ድንገት የሚከሠቱ አለመግባባቶችና አለመግባባቶቹን ለመፍታት ወይም አጣርቶ ተገቢውን አስተዳደራዊ ውሳኔ ለመስጠት የሚደረገው ሰፊ አቅምና ጊዜ የሚጠይቅ የሥራ ሂደት በዕቅድ የተያዙ ተግባራትን በታቀደው መሠረት ለመፈጸምና ለማስፈጸም የራሳቸው የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው ባይቀርም በረድኤተ እግዚአብሔር ለቤተ ክስርቲያን አንድነት፣ ሰላምና ብልጽግና የቀና አመለካከትና ቁርጥ ዓላማ ካላቸው የሀ/ስከቱ አስተዳዳር አባላት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ምእመናንና የሰ/ት/ቤት አባላት እገዛና ተባባሪነት ጋር ቀላል ግምት የማይሰጣቸውና ለቀጣይ የሥራ ጊዜ ምቹ ሁኔታዎችን ያስገኙ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል። ጥቂቶቹን እንደሚከተለው እናቀርባለን።

1.ሀገረ ስብከቱን የሀገሪቱ ሕግ በሚጠይቀው መልኩ በማኅበርነት ለማስመዝገብ የተጀመረውን ሕገ ደንብ የማዘጋጀትና የማጸደቅ እንቅስቃሴ በትኩረት በመከታተል ሕገ ደንቡ ከአጽዳቂው መንግሥታዊ መ/ቤት በተሠጡ የማስተካከያ አስተያየቶች መሠረት ተገቢው ማሻሻያ ተደርጎበት ለዕውቅና ሰጪው ፍ/ቤት የቀረበ ሲሆን በሳምንታት ዕድሜ ውስጥ አጽድቆ ማስረጃ ለመስጠት የአጭር ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶናል።
2. ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ መርሐ ግብሮችን ነድፎ በመተግበር የሀ/ስከቱ መሠረታዊ ችግር የሆነውን የገንዘብ እጥረት በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ ታስቦ የሀ/ስከቱ የል/ሰ/ጉ/ማ/መ እና የሂሣብ መምሪያ ኃላፊዎች የሚመሩት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር አዘጋጅ ጊዜያዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ የትምህርት ጉባኤ፣መጽሔት፣የቀን መቁጠሪያ፣ ሎተሪና የቃል ኪዳን ሰነድ የተካተቱበት መርሐ ግብር ተዘጋጅቷል። ሁሉንም የሀ/ስከቱ አካባቢዎች የሚያዳርስ በቂ ቅስቀሳ ማድረግ ባለመቻሉና አንዳንድ አድባራትም ምንም ዓይነት ተሳትፎ ለማድረግ ፈቃደኝነት ባለማሳየታቸው የተገኘው ውጤት ከዕቅዱ አንጻር አመርቂ ነው ባይባልም ከ8 ሺህ ኦይሮ በላይ ገቢ በማስገኘት የሀ/ስከቱን ዕለታዊ ወጪዎች ለመሸፈን የማይናቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። Read more

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የምሥራቅ፣ ምዕራብና ደቡብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የ፳፻፯ ዓ/ም የሥራና አገልግሎት ዘመን ዓመታዊ ሪፖርት

ሀገረ ስብከቱ በአዲስ መልክ ተዋቅሮ ሥራውን ከጀመረ ወዲህ ፳፻፯ ዓ/ም ፪ኛው የሥራ ዘመን ሲሆን በሥራ ዘመኑ ሀገረ ስብከቱን ከማደራጀት ጎን ለጎን የተቋቋመበትን መንፈሳዊ ተልዕኮ በአግባቡ በመወጣት በሥሩ ለሚያስተዳድራቸው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትናትና ለሕዝበ ክርስቲያኑ አልፎ ተርፎም ለመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት አቅምና ሁኔታ በፈቀደው መጠን የሥራና የአገልግሎት መሰናክል የሆኑ ሁኔታዎችን በብዙ ትዕግሥትና በመንፈሳዊ ጥበብ በማለፍና በማሳለፍ በዓመቱ ሊያከናውናቸውን ያቀዳቸውንና በዕቅድ ውስጥ ባይያዙም አስፈላጊ ሆነው የተገኙ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፤ አበረታች ውጤትም ተገኝቷል።
ከተከናወኑትም ተግባራት መካከል የሚከተሉት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡

1. አድባራት ከአስተዳደር ብልሽት፣ ከገንዘብና ንብረት ብክነት የጸዳና መግባ ባትና መተማመን የሰፈነበት ተመሳሳይ የአስተዳደር ሥራ አፈጻጸም ስልት እንዲከ ተሉ ለማስቻል በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ሥራ ውስጥ ኃላፊነትና ድርሻ ያላቸው የሰ/ጉ አባላት የቃለ ዓውዲ ሕገጋት፣ የአስ ተዳደር ሥራ አፈጻጸምና የሂሣብና ንብረት አያያዝ ሥልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ በታቀደው መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ በጀርመን ለሚገኙ አድባራት የካቲት ፯ ቀን ፳፻፯ ዓ/ም የሙሉ ቀን ሥልጠና በሀ/ስከቱ ጽ/ቤት በተሳካ ሁኔታ የተሰጠ ሲሆን ሥልጠናውን የተከታተሉ ከ፶ በላይ የሚሆኑ የ፱ አ/ክናት ተወካዮች በሥልጠ ናው ጠቃሚ ዕውቀትና ልምድ መቅሰ ማቸውን ገልጸዋል። ተሳታፊዎቹ የሥል ጠናው ማንዋል ታትሞ እንዲሠጣቸው በጠየቁት መሠረትም ታትሞ ለአድባራት በነፃ እንዲታደል የተደረገ ሲሆን ሥል ጠናው በቀጣዩ ዓመትም በሌሎች የሀ/ስከቱ አካባቢዎች ይቀጥላል።

2. ሀ/ስከቱ ምንም እንኳ በቤተ ክርስቲያኒቱ ወሳኔ ሰጭ አካል ፈቃድና ዕውቅና የተቋቋመ ሕጋዊ አካል ቢሆንም በአውሮፓ ሀገሮች ውስጥ በኦፊሲያል ለመንቀሳቀስ፣ ለመደራጀትና አጥቢያዎችንና መሰል ተቋማትን ለማደራጀት በአንድ የአውሮፓ ሀገር በሕጋዊ ማኅበርነት መታወቅና መመዝገብ ስላለበት ማኅበሩን ለማቋቋም የሚያስችል ቃለ ዓዋዲን መሠረት ያደረገ የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና በጀርመንኛ የተዘጋጀ ሲሆን ሕገ ደንቡ በአድባራት አስተዳዳሪዎችና የምእመናን ተወካዮች በተገኙበት ዓመታዊ ጉባዔ ከታየ በኋላ ለሚመለከተው መደበኛ ፍ/ቤት ቀርቦ እንዲ ጸድቅና ሥራ ላይ እንዲውል ይደረጋል። Read more